
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 07/2013 ዓ.ም (አብመድ) ከ80 ዓመታት በላይ ያስቆጠረውና በአደገኛነቱ የሚታወቀው የሊማሊሞ መንገድ ተለዋጭ ግንባታ እየተሠራለት መሆኑን ከአሁን በፊት መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የሊማሊሞ መንገድ በኢትዮጵያ ውስጥ አስቸጋሪ ከሚባሉ መንገዶች ከግንባር ቀደሞቹ ይጠቀሳል፡፡
የሊማሊሞ ተለዋጭ መንገድ መካከለኛው ኢትዮጵያን ከሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይና ኤርትራ ጋር የሚያገናኝ ትልቅ መንገድ ነው፡፡ የመንገዱ ጠመዝማዛነትና ከዕድሜው አንጻር ለአሽከርካሪዎችና ለመንገደኞች ምቾት አይሰጥም፡፡ መንገዱ ጥገና እንዲደረግለት ወይም ተለዋጭ መንገድ እንዲሠራለት በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲቀርብ ነበር፡፡
ከ2 ቢሊዮን 142 ሚሊዮን ብር በላይ የተመደበለት የሊማሊሞ ተለዋጭ መንገድ ጥር 2011 ዓ.ም ነበር የግንባታ ሥራው የተጀመረው፡፡ መንገዱ በደባርቅና በዛሪማ በሁለት በኩል እንደሚሠራ ከዚህ በፊት መዘገባችንም ይታወሳል፡፡
በቻይናው ‹ቤይጂንግ ኧርባን ኮንስትራክሽን ግሩፕ› ተቋራጭ ድርጅት ነው እየተገነባ ያለው፡፡ የባንግላዲሹ ‹ቢ ሲ ኤል› እና ሀገር በቀሉ ‹አይኮን› ደግሞ አማካሪዎች ናቸው፡፡
በአስፓልት ኮንክሪት ደረጃ እንደሚገነባ የተገለፀው የደባርቅ-ዘሪማ ተለዋጭ የሊማሊሞ መንገድ ሥራ ለማጠናቀቅ አራት ዓመታት ዕቅድ ተይዞለታል፡፡ ይህ መንገድ ታዲያ በተባለለት የጊዜ ገደብና ጥራት እየተከናወነ አለመሆኑ ነው የተነገረው፡፡ ‘‘የተቋራጩ አዲስ መሆንና የአቅም ጉዳይ፣ የአማካሪው ተነሳሽነት ደካማ መሆን ነው መንገዱን እያንጓተተው ያለው’’ ተብሏል፡፡ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የፕሮጄክቱ ከፍተኛ ኃላፊ እንደተናገሩት ‘‘የአማካሪ እንጂነሩ መንገዱን የማሠራት በቂ አቅም የለውም፤ በምን የመንገድ ፕሮጄክቱ እንደተሰጠው በራሱ ግራ የሚጋባ ነው፤ ትልቅ ፕሮጄክት ስለሆነ መምራት አይችልም’’ ነው ያሉት፡፡
የፕሮጄክቱን ሥራ አስኪያጅም ‘‘በቂ የሆነ ብቃት ያለው አይደለም’’ ነው ያሉት፡፡ ‘‘ሥራ አሥኪያጁ በሥራው ጥሩ አመራር ሲሰጥ ስላልነበረ ተባርሮ በምን ምክንያት እንደተመለሰ ሳይታወቅ ተመልሶ መጥቶ እየሠራ ነው’’ ብለዋል፡፡
የዞኑ የሥራ ኃላፊዎችም በርካታ መንገዶች በዞኑ ውስጥ ሲጓተቱ ይመለከታሉ ነገር ግን እየተከታታሉ ለሚመለከተው አካል መረጃ አይሰጡም፡፡ መንገዱን የእኛ ነው ብለው አይቆጣጠሩትም ነው የተባለው፡፡ በፕሮጄክቱ የማሽነሪ አቅርቦትም ሌላኛው ችግር እንደሆነ ተነስቷል፡፡ ፕሮጄክቱ እንዲሠራ በሚመቻችለት ሥፍራም በተገቢው መንገድ አይሠራም፡፡ ከካሳ ጋር በተያያዘም መንገዱ የማይገባውን የአርሶ አደሩን መሬት እየነካ አርሶ አደሩ ላይ ጫና ያሳድራል ተብሏል፡፡ በሠራተኛ ቅጥር ላይም ሌላ ችግር መኖሩን ነው የተናገሩት፡፡ ‘‘ፕሮጄክቱ በሚገባው ልክ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሥራ ዕድል አልፈጠረም፤ የሚቀጥራቸው እንኳን ለአካባቢው ተወላጆች አናሳ ደመወዝ ከሌላ አካባቢ ለሚመጡት ደግሞ ከፍ ያለ ደመወዝ ለተመሳሳይ ሥራ እየከፈ ኢ-ፍትሐዊ የሆነ ሥራ ይሠራልም’’ ብለዋል፡፡
መንገድ ሥራው ላይ ያሉት ችግሮች ከአሁኑ እልባት ካልተሰጣቸው በመንገዱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚፈጥሩም ነው የተመላከተው፡፡ ከአሁኑ መፍትሔ ካልተሰጠው በአካባቢው እንደሚገኙት ሌሎች የተጓተቱ መንገዶች ነው የሚሆነው ተብሏል፡፡ በዞኑ የደባርቅ-በለስ-መካነብርሃን-ቧኂት-ድል ይብዛ፣ የቡያ-ደጀች ሜዳ መንገዶች ለዓመታት በመጓተት የሚታወቁ ናቸው፡፡ በተለይ ከደባርቅ እስከ ድል ብዛ የሚሠራው መንገድ ከ10 ዓመታት በላይ የተጓተተ ነው፡፡ ‘‘ችግሮቹን በመለዬት ለመንገዶች ባለስልጣን ደብዳቤ አስገብተናል፤ ደካማ አፈጻፀም የነበረው አንድ ምክትል ሥራ አስኪያጅም እንዲነሳ አድርገናል፤ አሁንም ግን የሚመለከተው አካል ቦታው ድረስ መጥቶ መልስ እንዲሰጠን እንፈልጋለን’’ ብለዋል ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት የፕሮጀክቱ ከፍተኛ ኃላፊ፡፡
የደባርቅ-ሊማሊሞ-ዛሪማ ተለዋጭ መንገድ ረዳት ተጠሪ መሐንዲስ ኢንጂነር ታሪኩ ደሳለኝ ደግሞ ‘‘ተቋራጩ ቀጥታ ወደ ግንባታ አይገባም፤ መጀመሪያ ዲዛይን አድርጎ የሚሠራ መንገድ ነው’’ ብለዋል ስለፕሮጀክቱ ሲናገሩ፡፡ ይህ ደግሞ ጊዜ ሊፈጅ እንደሚችል አለማክተዋል፡፡ ‘‘የመስክ ጥናት አድርጎ፣ በኢትዮጵያ መንዶች ባለስልጣ አጸድቆ ሲጨርስ ነው ወደ ግንባታ ሥራ የሚገባው’’ ብለዋል፡፡
‘‘መንገዱ በመስከረም መጨረሻ 14 በመቶ መድረስ ይጠበቅበት ነበር፤ አፈጻጸሙ ግን 11 ነጥብ 5 በመቶ ደርሷል’’ ነው ያሉት፡፡ በኪሎ ሜትር ሲታሰብም 10 ኪሎ ሜትር ገደማ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ የዲዛይን ሥራዎቹ በጥሩ ሁኔታ ሄዷል ማለት ይቻላል፡፡ የቆረጣ ሥራው ግን በደባርቅ በኩል ብዙ እየሄደ አይደለም፤ በዛሪማ በኩል ግን የተሻለ እየተሠራ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ በደባርቅ በኩል የተፋሰስ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ‘‘ተቋራጩ በርካታ ማሽኖች አሉት፤ ገና ያልደረሱ መንገድ ላይ ያሉ ማሽኖችም አሉ’’ ነው ያሉት፡፡ በቅርቡ ወደ ፕሮጄክቱ እንደሄዱ የተናገሩት ኢንጂነር ታሪኩ የባንግላዲሹን አማካሪ ኢንጂነርም አቅም ለመለካት በቅርበት የሠሩ አለመሆናቸውንና ምን ዓይነት ብቃት እንዳለው መናገር እንደሚቸገሩ ለአብመድ ገልጸዋል፡፡ 2013 በጀት ዓመት ለፕሮጀክቱ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ኢንጂነሩ ‘‘ዲዛይኑ በጥሩ ሁኔታ ሄዷል፣ የአየር ንብረቱ ሁኔታ ተስማሚ ከሆነ እስከ ሰኔ ድረስ 50 በመቶ ለማድረስ ታቅዷል’’ ነው ያሉት፡፡
‘‘ተቋራጩ በቻይና ትልቅ ስም ያለው እንደሆነ ነው የሚነገርለት፤ የቴክኒክ ችግር ሊኖር ይችላል፤ ነገር ግን እውነት ለመናገር አቅም ያለው ተቋራጭ ነው’’ ብለዋል፡፡ እንዲያውም ፕሮጄክቱ ተስፋ ያለው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ‘‘ሥራውም ጥራት ያለው ነው፣ ለአብነት የሚያመርታቸው ቱቦዎች ጥሩ ናቸው’’ ሲሉም ቀደም ሲል የቀረቡ ቅሬታዎችን አስተባብለዋል፡፡ ወደ ኃላፊነት መጥተው በቆዩባት ጥቂት ሳምንታት በተቋራጩ ላይ የከፋ ነገር አለማዬታቸውንም ተናግረዋል፡፡ ‘‘ባለሙያ በማምጣት ጉዳይ ላይ ክፍተት ሊኖርበት ይችላል፣ በተለይ የአስፓልት ሥራ ሲጀመር ባለሙያ ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ይሄን ወደፊት የምናዬው ይሆናል’’ ነው ያሉት፡፡ በመንገድ ሥራው ላይ ተስፋ እንዳዩና ማሽኖችም ብዙዎች መሆናቸውን እንዲሁም ቴክኒካል የሆኑ ሰዎች እንደሚያስፈልጓቸው አመላክተዋል፡፡
የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደሪ ያለዓለም ፈንታሁን በዞኑ የሚገኙ በርካታ የመንገድ ፕሮጄክቶችን በመከታታል ረገድ ክፍተቶች እንደነበሩባቸው አምነዋል፡፡ ‘‘በዞኑ ያሉት ሁሉም የመንገድ ፕሮጄክቶች አፈጻጻማቸው ደካማ ናቸው’’ ብለዋል፡፡ በዞኑ ከ12 ዓመት በላይ የቆዩና በርካታ ጥያቄዎች የሚነሳባቸው መንገዶች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡ የሊማሊሞ ተለዋጭ መንገድም ችግር ያለበት እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ የዞኑ አስተዳደርም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንገዶችን እየተመለከተ ችግሮቹን በመለዬት ለሚመለከተው አካል እንዳሳወቀ ጠቁመዋል፡፡ ‘‘ችግሩን የክልሉ መንግሥትም እንዲያውቀው ደብዳቤ ልከናል’’ ብለዋል፡፡ የሊማሊሞን መንገድም እንደሚያዩና የሚነሱትን ችግሮች እንደሚለዩ የተናገሩት ዋና አስተዳደሪው በመንግሥት በኩል የሚጠበቀው እንዲደረግ ፕሮጄክቱን በሚይዘው በኩልም ችግሮች እንዲስተካከሉ ለማድረግ እየሠሩ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ‘‘ነገር ግን በሁሉም ዘርፍ ክፍተት አለ’’ ነው ያሉት፡፡
‘‘በአርሶ አደሩ ላይ የሚደርሱ ጫናዎችና በአርሶ አደሩ በኩል ያለውን ችግርም ዐይተን ማስተካካያ እንሰጥበታለን’’ ብለዋል፡፡ በፕሮጄክቱ ላይ የሚነሳውን ችግር በተጨባጭ መረጃ ላይ ተመሥርተው እንዲስተካከል እንደሚሠሩም ዋና አስተዳዳሪው ጠቁመዋል፡፡ በዞኑ የሚሠሩ መንገዶችን በቶሎ እንዲጠናቀቁ ዞኑ መፍታት የሚገባውን ነገር በመፍታትና የሰላም ችግር እንዳይፈጠር በማድረግ በኩል ዞኑ በቁርጠኝነት እንደሚሠራም ነው የተናሩት፡፡ ተቋራጮችንም በመከታተል፣ ሐሳብ በመስጠትና የማያስተካክሉ ከሆነ ውል እስከማቋረጥ የሚደርስ ግፊት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ ‘‘የዞኑ አንገብጋቢ ጥያቄ የመንገድ ችግር ነው’’ ያሉት አስተዳደሪው ‘‘ቁልፍ ተግባር አድርገን እንሠራለን’’ ነው ያሉት፡፡
በሰሜን ጎንደር ዞን የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ችግሮችና መፍትሔዎች በተመለከተ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንን ምላሽ ይዘን በሌላ ዘገባ እንመለሳለን፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
