
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 07/2013 ዓ.ም (አብመድ) በዞኑ 11 ወረዳዎች ላይ በሚገኙ 37 ቀበሌዎችና ከ196 በላይ ጎጦች የአንበጣ መንጋ መከሰቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል፡፡
የዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ አበበ ጌታቸው እንደተናገሩት ከ11ሽህ ሄክታር በላይ ሰብል ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ የበርሃ አንበጣ መንጋው በሰብል ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስም ባሕላዊና ዘመናዊ የመከላከል ተግባር በመከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
የመከላከል ሥራው ውጤታማ እንዲሆን ክስተቱ በታየባቸው ወረዳዎች የአንበጣ መንጋው ቀን በሰብል ላይ እንዳያርፍ በመከላከልና መብረር በማይችልበት በምሽት ሰዓት ደግሞ የኬሚካል ርጭት እየተከናወነ መሆኑን ነግረውናል፡፡
የደረሱ ሰብሎችን በዘመቻ የመሰብሰብ ተግባርም እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ከሰሞኑ ከ300 በላይ የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ በቀወት ወረዳ የሰብል መሰብሰብ ዘመቻ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ ይሕንን ተከትሎም የከተማ ነዋሪዎች፣ የፀጥታ አካላት፣ የመንግሥት ሠራተኞች እና ክስተቱ ያልታየባቸው አጎራባች ወረዳ አርሶ አደሮች እና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የመርጫ ኬሚካልና የሰብል መሰብሰቢያ መሳሪያ ይዘው በመዝመት እስካሁን ድረስ 35 ሽህ 200 ሄክታር መሬት ላይ የተዘራ ሰብል ተሰብስቧል፡፡
በዘመቻ አንበጣ መንጋውን የመከላከሉና ሰብል ስብሰባው ሥራ ጥሩ ውጤት እንደተገኘበትም አቶ አበበ ጠቁመዋል፡፡
ምንጃር ሸንኮራ፣ ሀገረማርያም፣ አሳግርት፣ አንኮበር፣ ቀወት እና አጣዬን ጨምሮ በ16 ወረዳዎች በተለይ ጤፍ ለመሰብሰብ ደርሷል፤አቶ አበበ እንዳሉትም የአንበጣ ክስተት ባልታየባቸው ቦታዎችም የደረሱ ሰብሎችን በዘመቻ መሰብሰብ ያስፈልጋል፡፡ለዚህም ኅብረተሰቡ ተጨማሪ ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን የአንበጣ መንጋ የተከሰተው ከመስከረም 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ የመንጋው ቁጥር ከፍተኛ ጭማሬ ማሳየቱን አቶ አበበ ተናግረዋል፡፡ በተለይ በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ክስተቱ ከቁጥጥር ውጪ በመሆኑ ዛሬ የመጀመሪያ ዙር በአውሮፕላን የታገዘ ርጭት ተደርጓል፡፡
በሌሎች የዞኑ አካባቢዎችም በሰው ኃይል እና በተሸከርካሪ በመታገዝ ርጭት እየተደረገ ይገኛል፤የተሸከርካሪዎች ቁጥር ግን የሰው ኃይል እና የመከላከያ መሳሪያዎችን ለማጓጓዝ በቂ እንዳልሆኑ አመላክተዋል፡፡ ለዚህም ለክልሉ መንግሥት ጥያቄ ማቅረባቸውን ነው አቶ አበበ ያስታወቁት፡፡
ክልሉም ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚደረግ ምላሽ መስጠቱን ተናግረዋል፡፡ ሰብል በመሰብሰብና በመከላከል ሂደቱ ማኅበረሰቡ በዘመቻ ሊሳተፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ፎቶ፡- በስማቸው አጥናፍ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
