ከተማ አስተዳደሩ በፕላንና በህጋዊ የከተማ እድገት አቅጣጫ ብቻ እንድትማራ አጥብቀው እንደሚሰሩ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ተናገሩ።

186

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 06/2013 ዓ.ም (አብመድ) ከተማዋ በፕላንና በህጋዊ የከተማ እድገት አቅጣጫ ብቻ እንድትማራ አጥብቀው እንደሚሰሩ አዲስ የተሾሙት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ተናግረዋል።

በበዓለ ሲመታቸው ወቅት መልእክት ያስተላለፉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከተማዋ የውጭና የሀገር ውስጥ ዜጎች ለመኖሪያነት የሚመኟት ታይታ የማትጠገብ ናት ብለዋል። ከተማዋ በውብ የተፈጥሮ መስህብ የታደለች ድንቅ ከተማ ነችም ብለዋል። የተፈጥሮ ሙዚየምና የታሪክ ሙዳይ የሆነች ከተማ አምራና ደምቃ እንድትገኝ ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት ያገለገሉ ከንቲባዎች፣ሎሎች የስራ ኃላፊዎችና ነዋሪዎቿ ምስጋና እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

አሁን ከተማዋን የተረከቡት የስራ ኋላፊዎች ደግሞ ከቀደሞቹ መልካም መልካሙን እንደመነሻ በመውሰድና በማጠናከር ከተማዋ በውበቷና በታሪኳ እንድትቀጥል፣ ወጣቶች ስራ የሚያገኙባት፣ አዛውንቶች የሚጦሩባት፣ባለሃብቶች ሳይጉላሉ ሰርተው የሚያተርፉባት፣ ቱሪስት የሚጎርፍባት፣ አርሶ አደሮች የሚለወጡበትና ሰላም የሰፈነበት ተወዳጅ ከተማ እንድትሆን የህብረተስቡም የመንግስትም ታላቅ ፍላጎት መሆኑን ተናግረዋል።

ባሕርዳርን ማልማት የምንችለው በጋራ አመራርና በህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ ነውም ብለዋል። ይህንም ለማሳካት የከተማዋን የስራ ኃላፊ በችሎታ፣ በአላማና በብቃት እየመዘን እናደራጃለን ነው ያሉት ። ከተማዋ በፕላንና በህጋዊ የከተማ እድገት አቅጣጫ ብቻ እንድትማራ አጥብቀን እንሰራለን ብለዋል። ባሕርዳር በምንመኘው መንገድ እንደትለማ ከሕዝባችን ጋር ተቀናጅተን በትኩረት እንሰራለን ነው ያሉት።

የከተማዋን ወጣቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ የስራ እድል መፍጠሪያ መስኮችን አሟጠን ለመጠቀም ጥረት እናደርጋለን ብለዋል። ለከተማዋ ሕዝብ በግልፀኝነትና ተጠያቂነት ላይ የተመሰረተ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ከሕዝቡ ጋር በቅርበት እየተመካከርን እንሰራለን ብለዋል። የአርሶ አደሮችን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግር እንፈታለንም ብለዋል። ከተማዋን የኢንቨስትመንት መዳረሻና የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ በዘርፉ የሚታዩ እንቅፋቶችን ለመቅረፍ ከምሁራን፣ ከመንግስት ሰራተኛውና ከሌሎች አከላት ጋር በመቀናጀት ወቅቱ የሚጠይቀዉን ስራ እንፈፅማለን ነው ያሉት። ከተማዋ በከተማ ፕላንና በህግ የበላይነት ልትመራ የምትችለው የሁሉም ነዋሪ ፍላጎት በፍትሃዊነት ሲስተናገድ ብቻ ነው ብለዋል።

የከተማውን ፈጣን እድገት ግምት ውስጥ ያስገባ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ የእለት ከእለት ስራዎች ይሆናሉ ነው ብለዋል። ስራዎችን ለመፈጸም የሚያስችል ለህዝብ ተደራሽ የሆነ በስነምግባር የተናፀ ቅቡልነት ያለው አመራር በሁሉም መስክ መፍጠር ዋነኛ ጉዳይ መሆኑን አመላክተዋል። የአመራር አቅም ግንባታና ስምሪትም ይከናወናል ነው ያሉት። የከተማው ህዝብም ንቁና ቀና ተሳትፎ እንዲያደርግም ጠይቀዋል። በህዝቡ ሙሉ ድጋፍ ከተማዋን የበለጠ እናስውባታለንም ብለዋል።

የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት በ4ኛ ዙር ምርጫ የ8ኛ ዓመት የሥራ ዘመን አስቸኳይ ጉባዔው አቶ አላዩ መኮንን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር የኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አድርጎ ሾሟል።
ተሿሚው በአዲሱ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳኅሉ(ዶክተር) አማካኝነት ዕጩ ሆነው የቀረቡ ናቸው።

ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ከአማራና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ መሪዎች ጋር ተወያዩ።
Next articleአዲሱ የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳኅሉ (ዶክተር) ማናቸው?