ከተማ አስተዳደሩ ዶክተር ድረስ ሳኅሉ ጎሹን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አድርጎ ሾመ።

273

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የ4ኛ ዙር ምርጫ የ8ኛ ዓመት የሥራ ዘመን አስቸኳይ ጉባኤው በቀድመው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ መሐሪ ታደሰ (ዶክተር) ምትክ አዲስ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሾሟል።

ምክር ቤቱ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አደርጎ የሾማቸው ዶክተር ድረስ ሳኅሉ “በሥራቸው ጠንካራና በትምህርት ዝግጅታቸውም አቅም ያላቸው ናቸው” ተብሏል። በአስቸኳይ ጉባኤው የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፍትሐነገሥት በዛብህ የተጀመሩ ሥራዎች ሳይንጣበጠቡ መፈፀም እንደሚገባቸው፣ የቤት መሥሪያ ቦታ ያላገኙ የቤት ማኅበራት እልባት እንዲሰጣቸው፣ በከተማ መስፋፋት የተነሱ አርሶ አደሮች በዘላቂነት እንዲቋቋሙ፣ የባሕር ዳር የዘላቂ የውኃ አገልግሎት እንዲሻሻልና የሥራ ዕድል ፈጠራና የሥራ እድል ፈላጊ አለመመጣጠን በትኩረት እንዲሠራበት አሳስበዋል።

የአገልግሎት አሰጣጥ ቢሮክራሲ እንዲስተካከልም አሳስበዋል። ሕገ ወጥ ግንባታና የኑሮ ውድነት በትኩረት ሊሠራባቸው የሚገቡ መሆናቸውንም አፈ ጉባኤው አመላክተዋል። የምክር ቤት አባላትም “ከተማ አስተዳደሩ በከተማዋ ተቀምጦ የሕዝቡን ችግር ቀን በቀን እየተከታተሉ የሚፈቱ ከንቲባ ያስፈልገናል ነው” ያሉት። “ምክር ቤቱ ከንቲባ ይሾማል ሲወርድ ግን እያወቅን አይደለም፤ የቀድሞው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ የወረዱበት ምክንያት ይነገረን?” ብለዋል። የክልሉ መንግሥት ለከተማዋ ያለው ዕይታ እንዲስተካከልና የከተማዋ ከንቲባዎች ቶሎ ቶሎ መነሳት ችግር እንደሆነም አንስተዋል።

የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር የብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተመሥገን በላቸው የቀድሞው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በነበሩበት ወቅት ተግባብቶ መሥራት እንደነበር አስታውሰዋል። “የክልሉን መንግሥት አስፈቅደው ወደውጭ ሀገር ሄደዋል። ሁለት ወር ከ15 ቀን በሥራ ገበታቸው አልተገኙም። እንዲመለሱም የጊዜ ገድብም ተቀምጦላቸው ነበር። ነገር ግን መመለስ አልቻሉም” ተብሏል። በዚህም ከኃላፊነት መነሳታቸው ተገልጿል።

ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየበረሃ አንበጣ መንጋውን ለመቆጣጠር በቀን 80 ሺህ ሄክታር መሬት ርጭት ማካሄድ እንደሚያስፈልግ የኮምቦልቻ ዕፅዋት ጥበቃ ክሊኒክ አስታወቀ፡፡
Next articleበቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከተፈጸሙ ጥቃቶች ጋር በተያያዘ 504 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ።