
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 06/2013 ዓ.ም (አብመድ) በምሥራቅ አማራ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን የበርሃ አንበጣ መንጋ በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር በቀን 80 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ርጭት ቢያስፈልግም እየተረጨ ያለው ግን ከ20 ሺህ ሄክታር አይበልጥም ተብሏል፡፡
የአየር ላይ ርጭቱን ለማከናወን በቀጣናው ሁለት የአውሮፕላን ማረፊያ ቢዘጋጅም በቅርቡ ይገባሉ የተባሉት ሄሊኮፕተሮች ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ አልደረሱም፡፡ መንጋው እያደረሰ ያለው ጉዳት ፀሐይና ብርዱን፣ በጋና ክረምቱን፣ አቀበትና ቁልቁለቱን ተቋቁሞ መሬቱን እና ፈጣሪን አምኖ ዘር ለበተነው አርሶ አደር መላ ከሰማይ በላይ ርቆበታል፡፡
የዓመት ልፋቱ በሰዓታት ልዩነት ብቻ መና ሲሆን ቆሞ እያየ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አንበጣው ከየትም ይምጣ የት ችግሩ እንደችግር መኖሩ ያንገበገባቸው ሁሉ መውጫ ቀዳዳ ያሉት ዘዴ እስካሁን የረባ ለውጥ አላሳየም፡፡ የሥርጭት ዓድማሱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ፣ አንዱ መንጋ ሲጠፋ ሌላው መንጋ እየተተካ፣ የሚጎዳው ሰብል ሲጨምር የሚወረረው መሬት ሲሰፋ እየተስተዋለ ነው፡፡
የበርሃ አንበጣ መንጋ ስርጭቱን ለመቆጣጠር ያስችላሉ ተብለው ተስፋ ከተጣለባቸው መንገዶች አንዱ የአየር ላይ የኬሚካል ርጭት ነው፡፡ ከሰሜን ሽዋ ምንጃር ሸንኮራ እስከ ሰሜን ወሎ ራያ ቆቦ ያሉት ወረዳዎች የአፋር ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ሁሉ የጥቃቱ ሰለባ እየሆኑ መጥተዋል፡፡
በዚህ ሰፊ መልክአ ምድራዊ አካባቢ የተሰገሰገውን የአንበጣ መንጋ ለመቆጣጠር ኮምቦልቻ እና ሽዋ ሮቢት ከተሞች ለዚሁ ዓላማ አገልግሎት የሚሰጡ ሁለት የአውሮፕላን ማረፊያዎች ተዘጋጅተዋል፡፡ የኮምቦልቻ ዕፅዋት ጥበቃ ክሊኒክ ዳይሬክተር ሙሐመድ ይመር “የበርሃ አንበጣው የተከሰተበት አካባቢ ሰፊ በመሆኑ ለሁለቱም የአውሮፕላን ጣቢያዎች ሁለት የቅኝት ሄሊኮፕተሮች እና አራት የርጭት አውሮፕላኖች ያስፈልጋሉ” ብለዋል፡፡ አሁን ላይ ግን በሥራ ላይ ያለችው አንድ ሄሊኮፕተር ብቻ መሆኗን ነግረውናል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ መረጃ በቀን አምስት ጊዜ በረራ ይካሄዳል፤ በአንድ ዙር ርጭት 4 ሺህ ሄክታር መሬት ይሸፈናል፤ በቀን 20 ሺህ ሄክታር ብቻ የኬሚካል ርጭት እየተደረገ ነው፡፡ አሁን ካለው የሥርጭት ፍጥነት እና ስፋት አንፃር ግን በቀን 80 ሺህ ሄክታር መሬት የኬሚካል ርጭት ያስፈልገው እንደነበር ነው አቶ ሙሐመድ የጠቆሙት፡፡ የቅኝት ሥራውም በየአካባቢው በተቀመጡ ግለሰቦች እየተሠራ ነው ተብሏል፡፡
በየአካባቢው የድረሱልን ድምፅ ቢኖርም ሰብል እየጎዳ ላለ እና ሥርጭቱ ከፍተኛ ለሆነ አካባቢ ቅድሚያ እየተሰጠ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በምድር የሚካሄደው የኬሚካል ርጭት እንዳልተቋረጠ ተናግረዋል፡፡ በቅርቡ ሁለት የርጭት አውሮፕላኖች እና አንድ የቅኝት ሄሊኮፕተር ባለፈው ረቡዕ ኮምቦልቻ ይደርሳሉ ቢባሉም እስካሁን ግን እንዳልደረሱ አቶ ሙሐመድ ነግረውናል፡፡
“አንድ የርጭት አውሮፕላን አዲስ አበባ መግባቷን ሰምተናል ነገር ግን የርጭት መሣሪያ ስላልተገጠመላት እሱ ተገጥሞ እስኪመጣ እየጠበቅን ነው፤ በሀገር ውስጥ ያለ አንድ የቅኝት ሄሊኮፕተርም በቅርቡ ኮምቦልቻ ይገባል የሚል ተስፋ አለን” ብለዋል፡፡
ከአውሮፕላኑ እጥረት በተጨማሪም የርጭት አልባሳት እና ባለሞተር የመርጫ መሣሪያዎች እጥረት እንዳለም ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው – ከወልድያ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
