
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 06/2013 ዓ.ም (አብመድ) በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ባለው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሴክተር ጉባኤ በኢትዮጵያ ሕጋዊ የካዳስተር ሥርዓትን ቀልጣፋና ወጥ በሆነ መልኩ ለመተግበር የሚያስችል የመተግበሪያ ሶፍትዌር ተመርቋል።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በማኅበራዊ ገፁ እንዳስታወቀው በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የተሠራው ይኸው ሶፍትዌር የዜጎች የይዞታ መብት እንዲረጋገጥና በዘርፉ የሚታየውን ውስብስብ የሆነ አሠራር ግልፅ ቀልጣፋና አስተማማኝ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ተመልክቷል።
የመተግበሪያ ሶፍትዌሩን የመረቁት የተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ የሆኑ ሴት ሚኒስትሮች የመተግበሪያው እውን መሆን ከመሬትና ተያያዥ ከሆኑ ጉዳዮች ጋር ለሚስተዋሉ ብልሹ አሠራሮችና እንግልቶችንም ለማስቀረት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡ በፍጥነት ወደ ተግባር መግባት እንዳለበትም አመላክተዋል።
የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ “የመሬት ምዝገባ ጉዳይ ኅብረተሰቡን ያማረረ ለኪራይ ሰብሳቢነት ያጋለጠና ስንቸገርበት የቆየ ጉዳይ ነው” ብለዋል፡፡ ይህንን ሊፈታ የሚችል ሶፍትዌር ተሠርቶ ይፋ መደረጉ ትልቅ እፎይታ መሆኑንም አመላክተዋል።
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ጫልቱ ሰኒ ጉዳዩ ውስብስብና ብዙ ኅብረተሰብና መንግሥትም ጭምር ሲቸገርበት የቆየ፣ አሰልቺ የሆነ ቢሮክራሲ ያለበት፣ ሀብትንም ያባከነና በተጨባጭ ለውጥ ያልመጣበት እንደነበር አስታውቀዋል፡፡ የመተግበሪያው እውን መሆን አስፈላጊ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
“ችግሩ በስፋት ስለሚታወቅ ይህ መተግበሪያ ውሎ ሳያድር ወደ ተግባር መለወጥ አለበት” ያሉት ደግሞ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ናቸው፡፡ መተግበሪያው በማዘጋጃ ቤቶች ያለውን እንግልት የሚፈታና ኅብረተሰቡን የሚያረካ አገልግሎት ለመስጠት ቁልፍ ሚና እንደሚኖረውም ዶክተር ሂሩት ተናግረዋል።
የልማትና ፕላን ኮሚሽነር ፍፁም አሰፋም (ዶክተር) ሲስተሙ አልቆ ለምረቃ በመብቃቱ መሬትን እንደ ትልቅ ሀብት እንዲታይ የሚያደርግ፣ ተገማች አሠራርን የሚዘረጋና ሕጋዊ ማረጋገጫ መስጠት የሚያስችል በመሆኑ በፍጥነት ወደ ተግባር ገብቶ ለማየት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። ኅብረተሰቡ እንደ አገልጋዩ መልካም ፈቃድ የሚስተናገድበት ረጅምና አሰልቺ ሂደት ባለውና ዘመናዊ አሠራርን ለማስፈን በሚረዳ ሲስተም መታገዙ ሕጋዊና ማኅበራዊ ፍትሕን በማስፈን ትልቅ ዋጋ እንዳለውም ተናግረዋል።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር አይሻ መሀመድ (ኢንጅነር) በበኩላቸው መተግበሪያውን ከተሞች ለማስጀመር ዝግጅት እንዲያደርጉና በፍጥነትም ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራ ገልፀዋል። “ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ኅብረተሰቡ ስለአሠራሩ ማወቅ እንዲጀምርም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ይሠራሉ” ብለዋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
