
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 06/2013 ዓ.ም (አብመድ) በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር አብመድ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ከምንም በላይ ለሰላምና ፀጥታ መስፈን ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የአንከሻ ጓጉሳ ወረዳ ነዋሪው አቶ ሰዋገኝ ይስማው የቀበሌ አደረጃጀት በመፍጠር እና ከእነርሱ የመቆጣጠር አቅም በላይ የሚሆኑ ወንጀሎችን ለፀጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት አስተማማኝ ሰላም እንዲፈጠር ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ነግረውናል፡፡
ምንም ወንጀል ቢፈጠር ከአካባቢው ማኅበረሰብ የሚደበቅ ነገር ስለማይኖር የወንጀሉን ፈጻሚ በፍጥነት መቆጣጠር እየተቻለ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ፀጥታውን ለማወክ የሚሠሩ አካላት እንኳን የአካባቢውን ጠንካራ አደረጃጀት ስለሚመለከቱ ወደዚህ ተግባር እንደማይገቡም ነው የተናገሩት፡፡ “በአካባቢያችን ያለው ሰላም እና መረጋጋት ለኢትዮጵያ ተምሳሌት ይሆናል” ብለዋል አቶ ሰዋገኝ፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪ የእንጅባራ ከተማ አስተዳደር 01 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሙሉጌታ ወርቁ ለአካባቢያቸው ሰላም መስፈን ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች እና የፀጥታ አካላት በቅንጅት መሥራታቸው ለአካባቢው ሰላም የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ግጭት ከመከሰቱ በፊት ስለግጭቱ መነሻ እና መፍትሔ በአስተውሎት የሚያመዛዝንና በአደረጃጀት የተዋቀረ ማኅበረሰብ መኖሩም ለአካባቢው ሰላም መረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አቶ ሙሉጌታ ነግረውናል፡፡
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የሰላም እና የሕዝብ ደኅንነት ግንባታ መምሪያ ኃላፊ ትዛዙ አበበ በብሔረሰብ አስተዳደሩ ስጋት በሚታይባቸው አካባቢዎች ለፀጥታ ኃይሉ በተለየ የግንዛቤ አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት የሥራ ሥምሪት እንደተደረገ ተናግረዋል፡፡ በብሔረሰብ አስተዳደሩ ጓንጓ፣ ዚገም እና አየሁ ጓጉሳ ወረዳዎች ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር የሚዋሰኑ እና ሕዝቦቹ በጋራ እንደሚኖሩ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
የፀጥታ ችግር እንዳይኖር በጋራ እና በትኩረት እየሠሩ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ መደበኛ የሕዝብ አደረጃጀት፣ የሰላም ኮሚቴ፣ የፀጥታ ምክር ቤት፣ የወንጀል መከላከል ኮሚቴ እና የፀጥታው አካላት በጋራ በመሆን ያካባቢውን ሰላም ለመጠበቅ ቅድመ መከላከሉ ላይ እንደሚያተኩሩም ገልጸዋል፡፡ ብሔረሰብ አስተዳደሩ ጉሙዝን ጨምሮ ሌሎች ብሔረሰቦች በጋራ በፍቅር የሚኖሩበት እንደመሆኑ የፀጥታ ሥራውም ሁሉን ያሳተፈ እንዲሆን መደረጉንም ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
ይህ በመሆኑም በብሔረሰብ አስተዳደሩ ከዚህ በፊት ከነበረው የተሻለ ሰላም ማምጣት መቻሉን ገልጸዋል፡፡ አልፎ አልፎ ስርቆት፣ ድብደባ እና የመሳሰሉ ክስተቶች እንደሚስተዋሉ የተናገሩት አቶ ትዛዙ እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶችንም፣ በድንገተኛ ፍተሻ እና በቅኝት ቁጥጥር እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
