በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በንጹኃን ዜጎች ላይ ጥቃት በፈጸሙ አካላት ላይ የፌዴራል መንግሥት ርምጃውን አጠናክሮ እንዲቀጥል የአማራ ክልል ሰላም እና ደኅንነት ቢሮ አሳሰበ፡፡

467
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 04/2013ዓ.ም (አብመድ) በንጹሐን ላይ የተፈጸመውን ጥቃት የግለሰብ ግጭት እንደሆነ ተደርጎ በክልሉ ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ የተሰጠው መግለጫ ትክክል አለመሆኑን የአማራ ክልል አስታወቀ፡፡
 
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በንጹኃን ዜጎች ላይ በተፈጸመው ጥቃት አስመልክቶ የአማራ ክልል ሰላም እና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ ሲሳይ ዳምጤ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
 
ቢሮ ኃላፊው እንደገለጹት በአንድ ባልታወቀ ግለሰብ ጥቃት ተፈጸመ ተብሎ በአካባቢው የቀበሌ አመራር አስተባባሪነት ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት ተፈጽሟል፡፡ ይህንም ተከትሎ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ የግለሰብ ግጭት እንደሆነ አድርገው የሰጡት መግለጫ ትክክል አለመሆኑን አቶ ሲሳይ ገልጸዋል፡፡
 
 
ጥቃቱ የሕዝብ ለሕዝብ ሳይሆን ቀጣናውን ሰላም ለመንሳት ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች አጀንዳ የሚቀበሉ የሥራ ኃላፊዎች የፈጸሙት ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
 
 
ችግሩን የፌዴራል መንግሥት በትኩረት እየተከታተለው እንደሚገኝ የገለጹት ቢሮ ኃላፊው በመተከል የሚገኙ ነዋሪዎችን ብቻ ሳይሆን በክልሉ የሚኖሩ ዜጎችንም ተዘዋውሮ የመሥራት ሕገ-መንግሥታዊ ዋስትናቸውን ሊያስጠብቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ላይም ምርመራ ሊያደረግ እና አጥፊዎች ላይ ርምጃ ሊወሰድ አንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡
 
በዚህ ወቅት ችግሩን ለመፍታት በቂ የፀጥታ ኃይል ወደ አካባቢው ቢገባም የሰሊጥ መሰብሰቢያ ወቅት በመሆኑ ነዋሪዎች በተናጠል ጥቃት እየተፈጸመባቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይህንም አስመልክቶ የአማራ ክልል መንግሥት ከፌዴራል ጋር በጋራ እየሠራ እንደሚገኝ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰቡም ራሱን በማደራጀት ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በቅንጅት እንዲሠራ አሳስበዋል፡፡
 
በዳግማዊ ተሠራ
Previous article“የታጠቁ ሕገ ወጥ ኃይሎች እስካሉ ድረስ ሰላም ሊሰፍን አይችልም፡፡” ምሁራን
Next article“በአካባቢያችን ያለው ሰላም እና መረጋጋት ለኢትዮጵያ ተምሳሌት ይሆናል።” አብመድ ያነጋገራቸው የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ነዋሪዎች