
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 04/2013ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶክተር) የተመራ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን የበርሃ አንበጣ መንጋ የመከላከል እንቅስቃሴውን በቦታው በመገኘት እየተከታተለ ነው፡፡ ልዑኩ በሰሜን ወሎ ዞን የበርሃ አንበጣ በተከሰተባቸው አካባቢዎች እየተካሄደ ያለውን የመከላከል ሥራ ተመልክቷል፤ ከአርሶ አደሮች እና ባለሙያዎች ጋርም እየተነጋገረ ነው፡፡
ልዑኩ ዛሬ ረፋድ ላይ የበርሃ አንበጣ መንጋው የተከሰተባቸው የራያ ቆቦ ወረዳ ሁለት ቀበሌዎች 41 አዲስ ዓለም እና 06 መንደፈራ ተገኝቶ የመከላከል ሥራውን ምልከታ አካሂዷል፡፡ በቀበሌዎቹ አንበጣው በጤፍ እና ማሽላ ሰብሎች ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ አርሶ አደሮቹ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የመከላከል ሥራው ቢጠናከር የተሻለ እንደሆነ የመፍትሔ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ እናም የፀጥታ አካላት፣ ተማሪዎች፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እንዲሳተፉ እና የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ እንዲተባበሯቸው ማስተባበር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በሰሜን ወሎ ዞን ሦስት ወረዳዎች 35 ቀበሌዎች አንበጣው ተከስቷል፡፡ በዞኑ 20 ሺህ 470 ሄክታር መሬት ነው ጉዳት የደረሰበት፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -ከሰሜን ወሎ
