“መንግሥት በተደጋጋሚ የሚያወጣቸውን መግለጫዎች ወደ ተግባር ሊቀይር ይገባል፡፡” የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ነዋሪዎች

177
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 04/2013ዓ.ም (አብመድ) መንግሥት ከሰሞኑ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የንጹኃን ሕይወት ማለፉን ተከትሎ ጠንከር ያለ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል። በመሆኑም የንጹኃንን ሕይወት ለመታደግ የሰጣቸውን መግለጫዎች ወደ ተግባር መቀየር እንዳለበት ነው ለመተከል ዞን አጎራባች የሆኑ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ነዋሪዎች የጠየቁት።
 
በመተከል ዞን የንጹኃን ሕይወት በተደጋጋሚ እያለፈ ነው፡፡ ከትናንት በፊትም ንጹኃን በግፍ ተገድለዋል። ጥቃት የሚደርሰው ደግሞ በሥራ የደከመ ጎናቸውን ለማሳረፍ ሀገር አማን ብለው በተኙበት ነው። ይህ ጥቃት እንዲቆም መንግሥት በተደጋጋሚ የሚሰጣቸውን መግለጫዎች ወደ ተግባር እንዲቀይር ነዋሪዎች አሳስበዋል።
 
አቶ ብታሙ ዓይናለም የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ነዋሪ ናቸው፡፡ ከሰሞኑ በመተከል ዞን በደረሰው ጥቃት እጅጉን ስሜታቸው የተጎዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጥቃቱ የደረሰው የክልሉ እና የፌዴራል መንግሥት በአካባቢው ሕግ ማስከበር ባለመቻላቸው መሆኑን ጠቁመዋል። ጥቃት የሚደርሰው ከጀርባ በመሆን በሚገፋፉ አካላት በመሆኑ መከላከል ቢቻልና መርዶ መስማት ሊያበቃ እንደሚገባ ጠቁመዋል። “የጉሙዝ ማኅበረሰብ እጅግ አዛኝ እና ሩህሩህ መሆኑን አብረን ኖረን ዐይተናል” ሲሉ ገልጸዋል አቶ ሀብታሙ፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነዋሪዎች ራሳቸውን እንዲከላከሉ አቅም ለማጎልበት እንደሚሠራ የገለጹት በፍጥነት ወደ ትግበራ መግባት እንዳለበትም ተናግረዋል።
 
 
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የጓንጓ ወረዳ ነዋሪ ደግሞ በወረዳው የጉሙዝ ብሔር ተወላጆች ጋር በፍቅር እና በአብሮነት እየኖሩ መሆኑን ተናግረዋል።
 
“ጥቃቱ በርቀት ለሚኖሩ ሰዎች ቀላል ይመስላል ለእኛ ግን የእግር እሳት ሆኖብናል” ሲሉም የጥቃቱን ሰቆቃ ገልፀዋል። የጃዊ ወረዳ ነዋሪው አቶ ንጋቱ ዋሴ ደግሞ አሁን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት ለዘመናት ሁለቱ ሕዝቦች አብረው ሲኖሩ ተከስቶ የማያቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ የሁለቱ ክልሎች መንግሥታት ሁነኛ ውይይት በማድረግ ችግሩን ከምንጩ ማድረቅ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።
 
 
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሺባባው
Previous articleከጎጃም መስመር ወደ ወደ አዲስ አበባ የሚንቀሳቀሱ አሽከርካሪዎች ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ጥቃት እየተፈጸመባቸው መሆኑን ተናገሩ፡፡  
Next articleየደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ እገዛ እንደሚያስፈልጋቸው የሰሜን ወሎ ዞን አርሶ አደሮች ጠየቁ፡፡