ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 04/2013ዓ.ም (አብመድ) ከጎጃም እና ከጎንደር በደጀን በኩል ወደ አዲስ አበባ የሚንቀሳቀሱ የደረቅ ጭነት አሽከርካሪዎች ኦሮሚያ ክልል ውስጥ መንገድ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት እየደረሰባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አስተያየታቸውን ለአብመድ የሰጡ አሽከርካሪዎች እንደተናገሩት ችግሩ የተፈጠረው ከሱሉልታ እስከ ዓባይ በርሃ ድረስ ባለው በኦሮሚያ ክልል በሚያለፍ የፌዴራል መንገድ ላይ ነው፡፡
ቀደም ብሎ በየኬላው በሚደረግ ፍተሻ ሕጋዊ ባልሆነ መልኩ ክፍያ ይጠየቁ እንደነበርም አንስተዋል፡፡ ሥራቸውን ላለማቆም እና ግጭት ውስጥ ላለመግባት ይጠየቁ የነበረውን ሕገ-ወጥ ክፍያ ፈጽመው ሥራቸውን ሲያከናውኑ እንደነበርም ጠቅሰዋል፡፡
ከሰሞኑ ደግሞ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትን የፀጥታ ኃይል መለዮ የለበሱ ታጣቂዎች በትጥቅ የታገዘ ጥቃት መፈጸማቸውን ተናግረዋል፡፡ በተለይ መስከረም 30/2013 ዓ.ም ምሽት ላይ የመሣሪያ ተኩስ እንደነበር አስተያዬት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡ በዚህም የሰው ሕይወት ማለፉን፣ የቆሰሉ መኖራቸውን እና መኪናዎች መቃጠላቸውን አስታውቀዋል፡፡
በቅርብ እርቀት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ሲያደርጉ የነበሩ የኦሮሚያ ክልል የፖሊስ አባላትም በወቅቱ እንዳልነበሩ ጠቅሰዋል፡፡ እንደ አስተያዬት ሰጪዎቹ ቅሬታ የጦር መሣሪያ ሲተኮስም የክልሉ የፀጥታ አካላት ሚናቸውን በአግባቡ አልተወጡም፡፡ ይህም አስተያዬት ሰጪወቹን “ችግሩ በመንግሥት መዋቅር ጭምር የተደገፈ ነው” እንዲሉ እንዳስገደዳቸው ገልጸዋል፡፡
ችግሩ ‘‘ከመስከረም 30/2013 ዓ.ም በኋላ መንግሥት የለም ሲባል ከነበረው ጋር ሊያያዝ የሚችል ቢመስልም ሕገ-ወጥ እንቅስቃሰው ቀደም ብሎም ነበር’’ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ብሔርን መሠረት ያደረገ ዘለፋ እና ስድብ እየደረሰባቸው መሆኑንም አንስተዋል፡፡ ጥቃቱን የፈጸሙት መለዮ ለባሾች በመሆናቸውም ችግሩን ለመንግሥት የፀጥታ አካላት ለማሳወቅ እንደተቸገሩ ገልጸዋል፡፡
ለመንግሥት ግብር የሚከፍሉና የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ በጥቃቱ ምክንያት ግን ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን አልቻሉም፡፡ በዚህም ከባንክ የተበደሩትን ገንዘብ ለመክፈል እንደሚቸገሩ አስተያዬታቸውን ሰጥተዋል፡፡
መንግሥት ዋስትና እስከሚሰጣቸው ለመሥራት እንደሚቸገሩ ያነሱት አስተየዬት ሰጪዎቹ የሁለቱ ክልሎች እና የፌዴራሉ መንግሥት በአጥፊዎች ላይ የማያዳግም ርምጃ እንዲወሰዱ ጠይቀዋል፡፡ ከስጋት የጸዳ የትራንስፖር እንቅስቃሴ እንዲኖር በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገቡም ተናግረዋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል መንግሥት አስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ጅብሪል መሐመድን ለማነጋር በተደጋጋሚ ብንደውልም ስልክ ሊያነሱልን ባለመቻላቸው ሐሳባቸውን ማከተት አልቻልንም፡፡ የክልሉ መንግሥት የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሲሆን አብመድ ለማስተናገድ ዝግጁ ነው፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
