“የመከራዎቻችን ወቅት ነጋዴዎች እና የክፉ ቀኖቻችን አትራፊዎች ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል፡፡” የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር

118
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 04/2013ዓ.ም (አብመድ) የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር የገጠመውን ወቅታዊ የበረሃ አንበጣ መንጋ ወረርሽኝ ጉዳት ለመከላከል እና ተጎጂዎችን ለመደገፍ የሚያስችል የውይይት መድረክ ከኅብረተሰቡ ተወካዮችና ከባለድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል፡፡ ዞኑ ቀደም ብሎ የአንበጣ መንጋውን ለመከላከልና ተጎጂዎችን ለመደገፍ የሚያስችል የአጭር እና ረጂም ጊዜ እቅድ አዘጋጅቶ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባቱን አስታውቋል፡፡
 
 
መጠነሰፊ የሆነው የበርሃ አንበጣ መንጋ ከተከሰተባቸው ምሥራቃዊ የአማራ ክልል አካባቢዎች መካከል የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር አንዱ ነው፡፡ ዞኑ በ24 ወረዳዎች እና በ597 ቀበሌዎች የተዋቀረ ሲሆን የአንበጣ መንጋው በሦስት ወረዳዎች እና 15 ቀበሌዎች ላይ ተከስቷል፡፡ በተሁለደሬ እና አርጎባ ልዩ ወረዳ የአንበጣ መንጋውን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ሲቻል፤ በወረባቦ ወረዳ 12 ቀበሌዎች ላይ ደግሞ ጉዳት አድርሷል፡፡
 
43 ሺህ 73 ሄክታር በሚሆን ሰብል፣ የእንስሳት መኖ፣ ቁጥቋጦ እና ደን ላይ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ 13 ሺህ 61 ሄክታር በባህላዊ እና ቀሪውን በኬሚካል ርጭት ለመካላከል ጥረት ተደርጓል ተብሏል፡፡ የአንበጣ መንጋው የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ የተደረገው ጥረት ውጤታማ እንደነበርም ተጠቁሟል፡፡
 
በውይይቱ ከደሴ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ ተሳታፊዎቹ የተፈጠረውን ወቅታዊ ችግር ለመቋቋም የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ “ወቅታዊ ችግሩ የአርሶ አደሩ ቢመስለንም የከፋ ጉዳት የሚያስከትለው ግን በከተማ ነዋሪዎች ላይ ነው” ብለዋል፡፡ በተጎዳው ማሳ ላይ ቶሎ የሚደርሱ ሰብሎችን መተካት እንዲቻል፣ ለተጎጂዎች የሚደረገው ድጋፍ ተቋማዊ መዋቅር እንዲኖረው እና አጋጣሚውን ወደ ዕድል ለመቀየር መንግሥት አብዝቶ እንዲንቀሳቀስ በውይይቱ ተጠይቋል፡፡
 
ዞን አስተዳደሩ በአጭር ጊዜ እቅዱ የበረሃ አንበጣ መንጋው በተለያዩ አካባቢዎች እንዳይሠራጭ የመከላከል ሥራው ላይ ሙሉ አቅሙን አሟጦ እንደሚጠቀም ተገልጿል፤ ተጎጂዎችን የመደገፍ ሥራውም በተለያየ መንገድ ይከናወናል ተብሏል፡፡ በረጂም ጊዜ እቅዱ ደግሞ የውኃ አማራጮችን ማስፋት፣ ቶሎ የሚደርሱ አዝርዕት መተካት፣ የመስኖ አማራጮችን መጠቀም፣ ውኃ መሳቢያ ጄኔሬተር አቅርቦት እና መሰል እንቅስቃሴዎች እንደሚከናወኑም ተጠቁሟል፡፡
 
ችግሩ መከሰቱ የአደባባይ ሀቅ ሆኖ ሳለ የሕዝብን እና መንግሥትን ጥረት ወደጎን ብሎ የራስ ፍላጎትን ለማራመድ የሚደረግ ጥረት የትም እንደማያደርስ ዞን አስተዳደሩ አሳስቧል፡፡ “የመከራዎቻችን ወቅት ነጋዴዎች እና የክፉ ቀኖቻችን አትራፊዎች ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል” ብሏል፡፡ ለተጎጂዎች ድጋፍ ማድረግ ለሚፈልጉ አካላት ዞን አስተዳደሩ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ ኮሚቴ ማቋቋሙን ጠቁሞ ከሕጋዊ መስመር ውጭ ያሉ አደረጃጀቶችን ግን እንደማይቀበል አስታውቋል፡፡
 
በውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶክተር) ሕዝቡ ድጋፍ የሚፈልግበት ወቅት መሆኑን አንስተዋል፤ መደማመጥ እና ልዩነትን አቻችሎ መሥራት ተገቢ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ “እንኳን ችግሮቻችን ስኬቶቻችንም አጀንዳዎች ናቸው” ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ አሉባልታውን በመተው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ላይ ብቻ ማተኮር ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ለተጎጂዎች ድጋፍ ማድረግ የፈለጉ አካላት ካሉ ክልሉን እና ዞኑን ቀርበው በማናገር ቁሳቁስ ይዞ ተጎጂዎች ቀየ ድረስ ለማድረስ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያግዝም አስታውቀዋል፡፡
 
ዞኑ ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት የድጋፍ የባንክ ሒሳብ ደብተር ከፍቷል፡፡ የሒሳብ ቁጥሮቹ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1000347841106 እና ዓባይ ባንክ 2322116812071011 መሆናቸውን ይፋ ተደርጓል፡፡
 
 
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው – ከደሴ
Previous article“የምንመለከተው ሁሉ የእኛ ስለመሆኑ ማረጋገጫ የለንምና ቀን ከሌሊት ሳንሰለች መከላከል ይጠበቅብናል፡፡” የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶክተር)
Next articleፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በዚህ ሳምንት የተመረቀውን የእንጦጦ ፓርክን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጋር እየጎበኙ ነው፡፡