“የምንመለከተው ሁሉ የእኛ ስለመሆኑ ማረጋገጫ የለንምና ቀን ከሌሊት ሳንሰለች መከላከል ይጠበቅብናል፡፡” የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶክተር)

169

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 04/2013ዓ.ም (አብመድ) በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶክተር) የተመራ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ቡድንም የበረሃ አንበጣ መንጋ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ተዘዋውረው አርሶ አደሮችን አነጋግረዋል፡፡ በተሁለደሬ ወረዳ የ027 ኮትቻ ቀበሌ አርሶ አደሮች ላለፉት 20 ቀናት ባደረጉት ዘመቻ ሰብላቸውን ከመንጋው መታደጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ሙሃመድ ይማም ቡሽራ እና ሁሴን አቡየ የቀበሌዋ ነዋሪ አርሶ አደሮች ናቸው፡፡ አርሶ አደሮቹ ላለፉት 20 ቀናት ከቤታቸው ወጥተው ውሎ አዳራቸው በማሳቸው አካባቢ ሆኗል፡፡ በተለያዩ አደረጃጀቶች ቦታ ተከፋፍለው የሚጠብቁት አርሶ አደሮቹ ከቀበሌያቸው አልፈው አጎራባች ዞኖች አና ወረዳዎች ድረስ ዘልቀው የመከላከል ሥራውን ይሠራሉ፡፡ “አንድ ጊዜ ወደ አካባቢው ከገባ በርትተን ብንከላከል እንኳን መጠነኛ ጉዳት ማድረሱ አይቀርም” ብለዋል አርሶ አደሮቹ፤ ከመግባቱ በፊት መከላከል ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡ መንጋው በሚገኝበት አካባቢ ከሌሊቱ 9፡00 ጀምረው ከወረዳ እና ቀበሌ የግብርና ባለሙያዎች ጋር በመሆን የኬሚካል ርጭት ያደርጋሉ፤ ቀን ቀን ደግሞ መግቢያ በሮች ናቸው ብለው በገመቷቸው አካባቢዎች ጭስ ያጨሳሉ፤ የመኪና ጎማ ያቃጥላሉ እንዲሁም ሌሎች ባህላዊ የመከላከያ መንገዶችን ሲጠቀሙ ይውላሉ፡፡ ይህ የአርሶ አደሮቹ ቀን ከሌሊት የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል የሚያደርጉት ጥረት ነው፡፡

ቀበሌዋም እስካሁን ድረስ እየተከሰተ ባለው የበርሃ አንበጣ መንጋ ጉዳት ያልደረሰባት እና እጅ ያልሰጠች ሆናለች፡፡ ሰብላቸው ተሰብስቦ ወደቤት እስኪገባ ድረስ ዘመቻው እንደሚቀጥልም አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል፡፡ ኬሚካል መርጫ እና ሌሎች ግብዓቶችን በማሟላት መንግሥት ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡

“የኮትቻ ቀበሌ አርሶ አደሮች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች አጎራባች ዞን እና ቀበሌዎችም አርአያ ሆነዋል” ያሉት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ታደሰ ግርማ ናቸው፡፡ በዞኑ በአርጎባ፣ ተሁለደሬ እና ወረባቦ ወረዳዎች በሚገኙ 15 ቀበሌዎች የበረሃ አንበጣ መንጋው መከሰቱን አቶ ታደሰ ተናግረዋል፤ አርጎባ እና ተሁለደሬ ወረዳዎች እስካሁን ድረስ መንጋውን ሙሉ በሙሉ ሲቆጣጠሩ በወረባቦ ወረዳ 12 ቀበሌዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል፡፡ በተሁለደሬ ወረዳ የታየውን መልካም ተሞክሮ ወደሌሎች ቀበሌዎች እና ወረዳዎች ለማስፋት እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ ለታየው በጎ ተነሳሽነትም አርሶ አደሮች፣ በየደረጃው ያሉ የሥራ ኃላፊዎች እና ግንባር ቀደም የግብርና ባለሙያዎች ሊመሠገኑ እንደሚገባ የግብርና መምሪያ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

“ትናንት በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ባቲ ወረዳ ወዮ ፈላና ቀበሌ ተገኝቸ ተስፋ ቆርጨ ነበር” ያሉት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶክተር) “የእናንተ ጥረት እና ውጤት ደግሞ አሁንም ተስፋ እንዲኖረን ያደረገ ነው” ብለዋል፡፡ የተዘራው ሰብል እስካሁን ሳይወድም መቆየቱ ተአምር ሳይሆን የአርሶ አደሮቹ፣ የሥራ መሪው እና የግብርና ባለሙያዎች የተቀናጀ የልፋት ውጤት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ አርሶ አደሮቹ ዛሬ ባለው ተስፋ ሳይዘናጉ እስከመጨረሻው መረባበረብ እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋል፡፡ “የምንመለከተው ሁሉ የእኛ ስለመሆኑ ማረጋገጫ የለንምና ቀን ከሌሊት ሳንሰለች መከላከል ይጠበቅብናል” ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ፡፡ አርሶ አደሮቹ የጠየቁት ግብዓት በአፋጣኝ እንደሚደርሳቸው እና ከመንግሥት በኩል የበረሃ አንበጣ መንጋውን ለመከላከል ምንም የሚጎድል ነገር እንደማይኖር ቃል ገብተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -ከተሁለደሬ

Previous articleመንግሥት አፋጣኝ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ሰብላቸው በበርሃ አንበጣ መንጋ የወደመባቸው የባቲ ወረዳ አርሶ አደሮች ጠየቁ፡፡
Next article“የመከራዎቻችን ወቅት ነጋዴዎች እና የክፉ ቀኖቻችን አትራፊዎች ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል፡፡” የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር