መንግሥት አፋጣኝ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ሰብላቸው በበርሃ አንበጣ መንጋ የወደመባቸው የባቲ ወረዳ አርሶ አደሮች ጠየቁ፡፡

178

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 03/2013ዓ.ም (አብመድ) በምሥራቅ አማራ እና አፋር አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተው የበርሃ አንበጣ መንጋ በከፍተኛ ፍጥነት የአርሶ አደሩን ሰብል ሙሉ በሙሉ እያወደመ ነው፡፡ የአንበጣ መንጋው የከፋ ጉዳት ካደረሰባቸው አካባቢዎች ውስጥ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አንዱ ነው፡፡ በብሔረሰብ አስተዳደሩ በርካታ ወረዳዎች የሚገኙ ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ሰብላቸው በበርሃ አንበጣ ወድሟል፡፡

ፋጡማ ሰይድ በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ባቲ ወረዳ 011 (ወዮ ፈላን) ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ ፋጡማ ባለቤታቸው በሕይወት የሉም፤ ቤተሰቡን የሚያስተዳድሩት ተፈጥሮ አብዝታ ማምረትን በነፈገቻት አካባቢ በእርሻ ሥራ ላይ ተመሰማርተው ነው፡፡

በአካባቢው ማኅበረሰብ የቆየ መተሳሰብ እና ጥብቅ ማኅበራዊ ትስስር መሠረት የአርሶ አደር ፋጡማ እርሻ በዘካ እና በትብብር ነው የሚታረሰው፡፡ የመኸር ወቅቱ አካባቢው ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ከፍተኛ ዝናብ አገኘና የፋጡማ እርሻ በሙሉ በዘካ ታርሶ በሰብል ተሸፈነ፡፡ የእርሳቸው እና የአካባቢው ሰው ልፋት ውጤት የሆነው እሸት ግን ለልጆቻቸው እንኳን አልደረሰም፡፡ ማሳው ሁሉ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተከሰተው የበርሃ አንበጣ ሙሉ በሙሉ ወድሟል፡፡ ዛሬ ወይዘሮ ፋጡማ ከሳምንታት በኋላ ቤተሰቡ ስለሚመገበው የሚመለከተውን ሁሉ “አቤት” እያሉ ነው፡፡

በአካባቢው ተገኝተን ያነጋገርናቸው ወይዘሮ ፋጡማ “ከሁለት ሳምንታት በኋላ ቤተሰቤ በሙሉ አደጋ ውስጥ እንወድቃለን፤ በዚህ ሰዓት መንግሥትንም ሁለት ነገሮችን እንጠይቃለን፤ የዕለት ጉርስ እና ሰላም” ብለዋል፡፡ በአፋር እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ወንድማማች ሕዝቦች መካል በሚፈጠረው የወሰን ግጭት ምክንያት የተማረሩት ወይዘሮ ፋጡማ የሁለቱ ክልል መንግሥታት መፍትሔ እንዲያፈላልጉም ጠይቀዋል፡፡ “ለዘመናት ተዋልደንና ተዋድደን የኖርን ሕዝቦች ነን” ያሉት ወይዘሮ ፋጡማ ለበርሃ አንበጣው ቁጥጥር አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ግጭቱ እንቅፋት ሳይሆን እንዳልቀረም ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በአካባቢው የበርሃ አንበጣ መንጋ ተከስቶ እንደነበር ያወሱት ደግሞ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አህመድ ሐሰን ናቸው፤ በአካባቢው ተፈጥሮ የነበረው የፀጥታ ችግር የበረሃ አንበጣ መንጋን የመከላከል ሥራውን ገድቦት እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በወቅቱ እስከ ታች ድረስ ወርዶ የአንበጣ መንጋው እንቁላል በጣለበት አካባቢ ቁጥጥር ቢደረግ ኖሮ ችግሩ ላይባባስ እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡

“እንደ ብሔረሰብ አስተዳደር ስናየው የአንበጣ መንጋው ሰፊ ውድመት አድርሷል” ብለዋል አቶ አህመድ፡፡ ባቲ ወረዳ ብቻ ከሚገኙት 26 የገጠር ቀበሌዎች በ21 ቀበሌዎች የአንበጣ መንጋው ተከስቶ ሙሉ በሙሉ ማሳ ላይ ያለ ሰብል ማውደሙን ነግረውናል፡፡ የአንበጣ መንጋው ቁጥጥር ከብሔረሰብ አስተዳደሩ አቅም በላይ መሆኑንም አስታውቀዋል ዋና አስተዳዳሪው፡፡ ሀገር አቀፍ ድጋፍ የሚፈልጉበት ወቅት ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የአንበጣ መንጋው በሰብል ላይ ሙሉ በሙሉ ጉዳት ባደረሰባቸው አካባቢዎች አፋጣኝ የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አቶ አህመድ ገልጸዋል፡፡ የአንበጣ መንጋው ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመት እና መጠነ ሰፊ ጉዳት እንዳያስከትል አሁንም የመከላከል ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ መንግሥት የአየር ላይ የኬሚካል ርጭት እንቁላሉ በተፈለፈለበት አካባቢ እንዲያደርግም አቶ አህመድ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው- ከባቲ

Previous articleክርስቲያኖ ሮናልዶ የኮሮናቫይረስ ተገኘበት፡፡
Next article“የምንመለከተው ሁሉ የእኛ ስለመሆኑ ማረጋገጫ የለንምና ቀን ከሌሊት ሳንሰለች መከላከል ይጠበቅብናል፡፡” የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶክተር)