
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 03/2013ዓ.ም (አብመድ) ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ በዘንድሮው ዓመት አሁን ከያዘው በሦስት እጥፍ የሚበልጥ ውኃ እንደሚይዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶክተር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ እና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያይስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ በጋራ እያደረጉት ባለው ሁለተኛ ቀን ጉብኝታቸው የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ለመጎብኘት ጉባ ተገኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው የግድቡ ግንባታ ሂደት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ መመልከታቸውንም ገልፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ለተሳተፉና አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ አስተዋፅኦ ላደረጉ ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አሁን ያለበት ደረጃ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ኩራት መሆኑን ተናግረዋል።
እስካሁን የተሠራው ሥራ ትልቅ ስኬት ቢሆንም በስኬቶች ከመኩራራት በየጊዜው አዳዲስ ግቦችን በመቅረፅ ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ለመውሰድ እንደሚሠራም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት ግድቡ ከፍ እንዲል ማድረግና አሁን ካለው ውኃ ሦስት እጥፍ እንዲይዝ ለማድረግ የሚሠራ በመሆኑ ይህ ዓመት የግድቡ ዋነኛ ሥራ የሚሠራበት እንደሆነም ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በዚህ ዓመት ኃይል ማመንጨት የሚጀምሩ ተርባይኖች ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል። “ተርባይኖቹ ለስድስት ወራት ሙከራ ካደረጉ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ኃይል ወደ ማመንጨት ይገባሉ” ነው ያሉት።
የግድቡን የግንባታ ሂደት የጎበኙበት ምክንያት የሥራውን እንቅስቃሴ ለማየትና ወደ ፊት በግድቡ አካባቢ ለመሥራት ለታቀዱት ከተሞች የአመቺነት ሁኔታን ለማየት እንደሆነ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።
ግድቡ ሲሞላ ብዙ ደሴቶችን መፍጠር ስለሚችል ከወዲሁ ያንን እያዩ መዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
“የግድቡ ሁኔታ ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና የምታደርገው ጉዞ ውጤታማ እንደሚሆን ለሁሉም ወገን የሚያመላክት ነው” ያሉት ዶክተር ዐብይ “በየጊዜው ያንን እያረጋገጥን ስኬታችንን እውን ማድረጋችን አይቀርም” ማለታቸውን ኢብኮ ዘግቧል።
