
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 03/2013ዓ.ም (አብመድ) የፖለቲካ ማሸነፍያ ስልቶች የሰዎችን ሞት ከማስተናገድ ይልቅ ለሰዎች ጥቅም ዕድል የሚፈጥሩ መሆን እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡
በኢትዮጵያ በየወቅቱ የሚስተዋሉ የግጭት እና የጥቃት ዓይነቶች መልካቸውን እየቀየሩና ወቅት እየጠበቁ እየተባባሱ መጥተዋል፡፡ ከሁለት ዓመታት ወዲህ የየወቅት አጀንዳዎች በመሆናቸውም ሰብዓዊነት መብት ሳይሆን የዘውትር ተማፅኖ እየሆነ ነው፡፡ እንደሀገር በሰዎች ላይ የሚደርሰው ሥነ ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ ቢያስከትልም የብዙኃኑ ሰላም ወዳድነትና አስተዋይነት ግን የሚደነቅ እንደነበር አስተያዬት ሰጭዎች ተናግረዋል፡፡
ፖለቲካዊ ሴራዎችና የተገፋን ባዮች ሴራ ከሰዎች ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶች በላይ መደለል በመቻሉም ጥቃቱ እስከ ዛሬ ዕድሜ ማግኘታቸውን ሐሳብ ሰጭዎቹ ገልጸዋል፡፡
አስተያዬት ሰጭዎቹ በሀገሪቱ የሚከሰቱ ግጭትና ጥቃት መነሻዎችን እንደሕዝብ ለሰላም አስተዋጽኦ በማድረግ ሕግ የማስከበር ተግባራት ቅድሚያ እንዲሰጣቸው አሳስበዋል፡፡
በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ አብመድ ያነጋገራቸው የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ሰሜን ወሎና ምሥራቅ ጎጃም ነዋሪዎች ቅቡል ሐሳብ ሀገር እንዲመራ ዕድል መስጠት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
በሰሜን ወሎ ዞን የወልዲያ ከተማ ነዋሪው አቶ እያሱ ደሳለኝ “ሀገሪቱ ካለችበት የንጹሐን ጥቃት ለመላቀቅ ፖለቲከኞች ትንሽ ሊተባበሩ ይገባል” ብለዋል፡፡
“ፖለቲከኞች የሕዝብ ተጠቃሚነት ምህዋራቸው ሐሳብ እንጂ ዘር ወይም ሃይማኖት መሆን የለበትም” ያሉት አቶ እያሱ ሐሳብ ሀገር እንዲመራ፤ ሐሳብ ሀገር እንዲያበለጽግ፤ ሐሳብ ነገን ቀላል እንዲያደርግ ፖለቲከኞች ሥራቸውን ከእንጀራ ገመድነት በዘለለ በሐሳብ የበላይነት ላይ የተመሠረተ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡
“በየአካባቢው በሚፈጠሩ ጥቃቶችን የሚከላከሉ ሰዎች ላይ የሚፈጠረው ጥቃት እንደሕዝብ መተባበር እንዳይፈጠር የሚያደርገው ሕግ የማስከበር ሥራው በመንሻፈፉ ስለሆነ መንግሥት ኃላፊነቱን መውሰድ ይኖርበታል” ብለዋል አቶ እያሱ፡፡ ሕዝቡ የሐሳብ መሪዎችን “እኔን” እያለ የሚያስቀድም ፤ ሀገሬ የሚሉትን ሁሉ ከልቡ የሚከተል ቢሆንም ሕዝቡ የወደዳቸው ሐሳቦችን እየተከታተሉ በማጥፋት የሚከሰተው ጥቃት ደግሞ አለመረጋጋት እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሀገር እንደቤት በተስማሙ ማገሮች የተገነባች አድርገው እንደሚያዩ የተናገሩት የሰቆጣ ከተማ ነዋሪው መምህር ዓለም ተሾመ “የቤቱ ባለቤት እንደየወቅቱ ፀሐይና ዝናብ የሚያስገቡ ክፍተቶችን በኃላፊነት በማልበስ ችግሩን እንደሚፈታ ሁሉ በሀገር ጉዳይም ሁሉም ኃላፊነት በመወጣት ለክፍተቶቹ ሽፋን እንጂ መባባስ ምክንያት መሆን አያስፈልግም” ብለዋል፡፡ ከዚያ ይልቅ እያንዳንዱ ማገር ከሌላው ማገር ያለውን ግንኙነት በማዋደድ እንጂ በማራራቅ የቤቱን ችግር መፍታት እንደማይቻልም ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሐሳብ ሀገር እንዲመራ ዕድል መስጠት እንዳለባቸው ያሳሰቡት አቶ ዓለም ሐሳብ ሀገር እንዲመራ ዕድል መስጠት መጀመር ለችግሮች መፍትሔ ማስቀመጥና ለነገ መዳረሻ የጋራ እቅድ ላይ ርብርብ እንዲደረግ ዕድል የሚፈጥር እንደሆነ አመላክተዋል፡፡
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪው ዶክተር አየነው ማሞ ደግሞ በሀገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ ጥቃቶችን ለመግታት ሕዝቡ እንደሕዝብ ለሰላሙ ዘብ ለመሆን እንዲችል ሕግ የማስከበር ተግባሩ መቅደም እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ሰላም እንቅፋት በሆኑ ድርጊቶች ላይ እንደሕዝብ፣ እንደመንግሥት እና እንደተፎካካሪ ፓርቲዎች የመፍትሔ እርምጃ እንዲወስዱ ቁርጠኝነት ሊኖር እንደሚገባም ዶክተር አየነው አሳስበዋል፡፡ ግለሰባዊ መብት ሲከበር የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ መብቶች የመጠበቅና የተፈጥሮ ሀብቶችን የመጠቀም ዕድል እንደሚሰፋም አስታውቀዋል፡፡ የዴሞክራሲ መስፈን በመዘናጋት እና በፖለቲካ ሴራ ሰው እንዲጠፋ ዕድል መክፈት ባለመሆኑ ሕግ የማስከበር ሥራ እንቅልፍ የማያስወስድ ተግባር መሆን እንዳበለትም ዶክተር አየነው አመላክተዋል፡፡
አስተያዬት ሰጭዎቹ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መንግሥትም ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማስጠበቅ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ በሕግ የመጠየቅ መደላድሉን ሊፈጥር እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የፖለቲካ ማሸነፍያ ስልቶች የሰዎችን ሞት ከማምጣት ይልቅ ለሰዎች ዕድል የሚፈጥሩ እንዲሆኑ ሁሉም ፓርቲዎች እና የተሸናፊነት ሥነ-ልቦና ውስጥ ያሉ ኃይሎች ድልን በሰላማዊ የምርጫ ተሳትፎ ማረጋገጥ እንደሚገባቸውም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ
