በአማራ ክልል የወባ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን ኢንስቲትዩቱ አስታወቀ፡፡

561

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 03/2013ዓ.ም (አብመድ) በክልሉ በ2012 በጀት ዓመት የወባ ተጠቂዎች ከ2011 በጀት ዓመት ተጠቂዎች ቁጥር በ66 በመቶ ጨምሯል፡፡

ባለፉት ሦስት ወራትም ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች በወባ መጠቃታቸውን የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ ገልጿል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በ2019 (እ.አ.አ) ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው በ2018 (እ.አ.አ) 228 ሚሊዮን ሰዎች በዓለም ላይ በወባ ተጠቅተዋል፡፡ ከ400 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ከ5 ዓመት በታች ሕጻናት የችግሩ ሰለባ ሆነዋል፡፡ በዚህም በዓለም አጠቃላይ በወባ ሕይወታችው ካለፈው 67 በመቶ ሕጻናት እንደሆኑ ተመላክቷል፡፡

አፍሪካ ደግሞ ከፍተኛ የወባ ተጠቂ እንደሆነች ድርጅቱ ይፋ አድርጓል፡፡ በ2018 (እ.አ.አ) በዓለም በወባ ሕይወታቸው ካለፈው ሰዎች ውስጥ 85 በመቶ የሚሆኑት በ20 የአፍሪካ ሀገራት እና በህንድ የተከሰተ እንደሆነ መረጃው ያሳያል፡፡ ነፍሰጡሮች እና ታዳጊዎች ደግሞ ይበልጥ ተጠቂዎች እንደሆኑ ድርጅቱ ገልጧል፡፡

በ2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ 1 ሚሊዮን ሰዎች በወባ ተጠቅተው ነበር፡፡ በ2012 ዓ.ም ቁጥሩ ወደ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ በ2012 በጀት ዓመት በክልሉ ከ400 ሺህ በላይ ሰዎች በወባ በሽታ ተጠቅተዋል፡፡ ይህም በ2011 በጀት ዓመት ከነበረው የተጠቂዎች ቁጥር 66 በመቶ ጨምሯል፡፡ ባለፉት ሦስት ወራት ደግሞ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች በወባ በሽታ ተጠቅተዋል፡፡ በክልሉ አብዛኛው ወረዳዎች ወባን ሪፖረት ቢያደርጉም 25 ወረዳዎች ወረርሽኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ከአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃ ያመለክታል፡፡

“ወባን ማጥፋት ከእኔ ይጀምራል” በሚል መሪ ሐሳብም እስከ ጥቅምት 5 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በሀገር አቀፍ ደረጃ የወባ ሳምንት እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የወባ አሁናዊ ሥርጭትን አስመልክቶ የምዕራብ ጎንደር ነዋሪዎችን አነጋግረናል፡፡ በዞ ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮች እንደገለጹት ባለፉት ወራት ከፍተኛ የሆነ የወባ ስርጭት ተከስቷል፡፡ ይህን ተከትሎ የፀረ ተባይ ርጭት ቢካሄድም እስከዛሬ ድረስ የአጎበር ስርጭት አለመካሄዱ የወባ ስርጭቱን ሙሉ በሙሉ ለመከላከል እንዳስቸገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ ሁለት ዓመት ላለፋቸው ወረዳዎች ፈጥኖ አጎበር ሊሠራጭ እንደሚገባም ነዋሪዎች አሳስበዋል፡፡

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወባ ፕሮግራም አስተባባሪ ማስተዋል ወርቁ እንደገለጹት ደግሞ የክልሉ መልክአ ምድር አቀማመጥ ለወባ መራቢያ ምቹ መሆን፣ የማኅበረሰቡ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ መቀነስ እና በአልጋ አጎበር አጠቃቀም ችግሮች ምክንያት ከሳምንት ሳምንት ከፍተኛ የሆነ የወባ ሕሙማን ቁጥር በክልሉ እየተመዘገበ ይገኛል፡፡ ባለፉት ሦስት ወራትም ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች በወባ መጠቃታቸውን አስተባባሪዋ ነግረውናል፡፡

በክልሉ 53 ወረዳዎች የኬሚካል ርጭት ለማካሄድ አቅርቦት ተጠይቋል፡፡ ይሁን እንጅ በኬሚካል አምራች ፋብሪከው የማምረት ውስንነት ምክንያት መቅረብ የቻለው ከተጠየቀው 75 በመቶ ብቻ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በ22ቱ ወረዳዎች በከፊል የፀረ ተባይ ኬሚካል ርጭት የተካሄደ ሲሆን በ9 ወረዳዎች ደግሞ ርጭት ማካሄድ አለመቻሉን አስተባባሪዋ ገልጸዋል፡፡

በ2013 በጀት ዓመት በክልሉ ለሚገኙ 55 ወረዳዎችም 4 ሚሊዮን አጎበር ቀድሞ ለማሠራጨት ለጤና ሚኒስቴር ቢጠየቅም ከመተማ፣ ፎገራ እና ገንዳ ውኃ ከተማ አስተዳድር ውጭ በግዥ መጓተት ምክንያት እከዚህ ወቅት ማሠራጨት አልተቻለም፡፡ ይህ ደግሞ የወባ መከላከል ሥራውን አስቸጋሪ እንደሚያደርገው አስተባባሪዋ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ነፍሰጡር እናቶች እና ከ15 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ይበልጥ በወባ ተጠቂ መሆናቸውን አስተባባሪዋ ገልጸዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በ2030 (እ.አ.አ) ወባን ለመቆጣጠር እና ለማስወገድ የሚያስችሉ ስልቶችን ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያም የዓለም ጤና ድርጅት አባል በመሆኗ የድርጅቱን ስልቶች ተግባራዊ በማድርግ ላይ ትገኛለች፡፡ በክልሉ ወባን ለማጥፋት በሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞኖች፣ ሰሜን ሸዋ ዞን እና ደሴ ከተማ አስተዳድር በመነሻነት ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ እየተሠራ ይገኛል፡፡

ወባን ለማስወገድ በአብዛኛው የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ የገለጹት አስተባባሪዋ ወባን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የተቀመጡ መርሆችን ተግባራዊ ለማድርግ ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ በክልሉ የንቅናቄ ሥራ እንደሚሠራ አስተባባሪዋ ገልጸዋል፡፡

ኅብረተሰቡ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራውን በተደራጀ መንገድ ማከናወን ካልቻለና መንግሥት የአጎበር፣ የኬሚካል እና የወባ መድኃኒት አቅርቦት መቆራረጥ ችግሮችን መፍታት ካልቻለ የወባ ስርጭቱ ከዚህ በላይ ሊጨምር እንደሚችል አስተባባሪዋ አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ
ምስል፦ ከድረገጽ

Previous articleየደኅንነት ፍተሻ መስፈርት አሟልቶ እንዳይገባ የተከለከለ ሰዉ አልባ በራሪ ቁስ (ድሮን) እንደሌለ የኢንፎርሜሽን መረበ ደኅንነት ኤጀንሲ አስታወቀ።
Next articleሐሳብ ሀገር እንዲመራ ዕድል መስጠት እንደሚያስፈልግ አስተያየት ሰጭዎች ተናገሩ፡፡