
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 03/2013ዓ.ም (አብመድ) የሚጠበቅበትን የደኅንት ፍተሻ መስፈርት አሟልቶ ወደሀገር እንዳይገባ የተከለከለ ሰዉ አልባ በራሪ ቁስ (drone) አለመኖሩን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሹመቴ ግዛዉ (ዶክተር) ገልጸዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ይህን የተናገሩት ዛሬ በኤጀንሲዉ ለጋዜጠኞች ስለተቋማዊ ሪፎርም እና ቀጣይ የአምስት ዓመት የትኩረት አቅጣጫ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት መድረክ ነዉ፡፡
የኤጀንሲዉ ዋና ዳይሬክተር እንዳሉት ሰሞኑን በማኅበራዊ ሚዲያዎች “ኤጀንሲዉ ለበረሃ አንበጣ መንጋ መከላከያ የሚሆን ድሮን ወደትግራይ ክልል እንዳይገባ ተደርጓል” የሚባለው ሐሰት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የደኅንነት ፍተሻ አሟልቶ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገባ የተከለከለ ድሮን አለመኖሩንም አስታውቀዋል፡፡
ድሮን ወደ ሀገር ወስጥ ሲገባ የራሱ የሆነ የአሠራር ሥርዓት እንዳለዉ ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ በኢትዮጵያ የተከሰተዉን የበረሃ አንበጣ መንጋ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የትግራይ ክልልን ጨምሮ የተለያዩ ክልሎች ድሮኖችን ለማስገባት ጥያቄ አቅርበዉ በመመሪያዉ መሠረት እየተስተናገዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሰሞኑን በማኅበራዊ ሚዲያ “ወደ ትግራይ ክልል ድሮን እንዳይገባ ተደርጓል” የተባለዉ ጉዳይም በመጀመሪያ ደረጃ ድሮኑ ለጥናት (research) እና ‘ሪቨርስ ኢንጂነሪነግ’ (Reverse engineering) ዓላማ በሚል የመጣ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ በመቀጠልም ድሮኑ ለጸረ-ዓረም ኬሚካል መርጫ ዓላማ እንደሚውል የተገለፀ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ ለበረሃ አንበጣ መንጋ መከላከል ዓለማ በሚል መጠየቁንም አንስተዋል፡፡
ኤጀንሲዉ በድሮኑ ላይ የደኅንነት ፍተሻ ባደረገበት ወቅት ድሮኑ የአጠቃቀም እና ተጓዳኝ ጉዳዮች መግለጫ ወይም ማኑዋል የሌለዉ ከመሆኑ ባሻገር ከእስራኤል እንደተላከ ቢገለጽም ምርቱ ግን ከቻይና እንደሆነ መታወቁን ገልጸዋል፡፡ ሆኖም የድሮኑ ትክክለኛ ዓላማ እና የሚሰጠዉን አገልግሎት የደኅንነት ተጋላጭነትን የሌለው መሆኑን ማጣራት የኤጀንሲዉ ኃላፊነት መሆኑ አስታውቀዋል፡፡
ከአጄንሲው የተገኜው መረጃ እንደሚያመላክተው ዋና ለአንበጣ መከላከል ተብሎ የተጠየቀው ድሮን የደኅንነት ፍተሻ አሟልቶ ባለመገኘቱ ፈቃድ ያልተሰጠው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
