“ለአርሶ አደሩ አሁን ካልደረስን መቼም አንደርስለትም።” የሰሜን ሸዋ ግብርና መምሪያ

272

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 03/2013ዓ.ም (አብመድ) በሰሜን ሸዋ ዞን የበረሃ አንበጣ መንጋ በሰብል ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የደረሱ ሰብሎችን በዘመቻ የመሰብሰብ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ዛሬም የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ እና የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች በሸዋሮ ቢት ከተማ አስተዳደር እና ቀወት ወረዳ ጤፍ እየሰበሰቡ ነው፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ መሠረት ኃይሌ እንዳሉት በዚህ ጊዜ ምንጃር ሸንኮራ፣ በረኸት፣ አንኮበር እና አንጾኪያን ጨምሮ በዞኑ 16 ወረዳዎች የቆላማ አካባቢዎች ጤፍ ሰብል ደርሷል፡፡ ማሾ ቀደድሞ ተሰብስቧል፤ ማሽላ ስንዴ እና ሌሎች ሰብሎች ግን ገና አልደረሱም፡፡ የበረሃ አንበጣ መንጋውን ከመከላከል ባለፈም የደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ እንደሚገባ መምሪያ ኃላፊዋ አሳስበዋል፡፡ “ለአርሶ አደሩ አሁን ካልደረስን መቼም አንደርስለትም” በማለት ሰብል በደረሰባቸው ወረዳዎች የሰው ኃይል እጥረት እንዳያጋጥም አጎራባች ወረዳዎች፣ የከተማ ነዋሪዎች እና የመንግሥት ሠራተኞች ከፍተኛ ርብርብ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅረበዋል፡፡ የዞኑ ሕዝብ አስተባባሪ ካገኘ በዘመቻው ለመሰማራት ዝግጁ መሆኑን በማንሳትም በየወረዳው ያሉ መሪዎች በንቃት እንዲያስተባብሩ አሳስበዋል፡፡

በዞኑ እስከ ትናንት ጥቅምት 2/2013 ዓ.ም ድረስ በዘጠኝ ወረዳዎች በ24 ቀበሌዎቸ ተከስቷል፡፡ ወደ 11 ሺህ የክታር መሬት መሸፈኑንም አንስተዋል፡፡ የበርሃ አንበጣን ለመከላከል ቀደም ብሎ ዝግጅት በመደረጉ ከ4 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነውን በባህላዊ እና በዘመናዊ መንገድ መከላከል ተችሏል፡፡ ባለሙያዎች እና ኅብረተሰቡ ከምሽት 1፡00 ጀምሮ በመብራት ያታገዘ ርጭት ማድረጋቸው የመከላከል እንቅስቃሴውን የተሻለ አድርጎታል፡፡

ከኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር እና ከአፋር ክልል አጎራባች ወረዳዎች ጋር በመናበብ እየተሠራ ቢሆንም በቀወት፣ ምንጃር ሸንኮራና ጣርማበር ወረዳዎች በ746 ሄክታር መሬት በሰብል ላይ ጉደዳት ማድረገሱን አስታውቀዋል፡፡ በሁሉም ወረዳዎች የደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ እንደሚገባም መምሪያ ኃላፊዋ አሳስበዋል፡፡ በተለይም የክስተቱ የሥጋት ቦታዎችን በመለየት ከፍተኛ ርብርብ እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡

በመከላከል ሂደቱ የፌዴራል እና ክልሉ መንግሥታት ጥሩ ድጋፍ ማድረጋቸውም ተነስቷል፡፡ ወይዘሮ መሠረት የወረርሽኙ ስርጭት የሚጨምር ከሆነ የአውሮፕላን ርጭት ለማድረግ የተጀመረ ተግባር መኖሩንም ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን የተሽከርካሪ እጥረት እና የመልክአ ምድሩ አለመመቸት በመኪና ለማሰስ እና ርጭት ለማድረግ ችግር ሆኗል፡፡ ለባለሙያዎች የአልባሳት አቅርቦት አለመኖሩም ተጠቅሷል፡፡

የአንበጣ መንጋው ሰብል ላይ እንዳያርፍ መከላከል፣ የደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ፣ በተረራራማ አካባቢዎች ካረፈ በኋላም ምሽት ላይ በመብራት ታግዞ ርጭት ማድረግ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መክረዋል፡፡ አርሶ አደሩ ማሳውን በንቃት እንዲከታተልም አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

Previous articleመንግሥት የበርሃ አንበጣውን ለመከላከል ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርግ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶክተር) አስታወቁ፡፡
Next articleየደኅንነት ፍተሻ መስፈርት አሟልቶ እንዳይገባ የተከለከለ ሰዉ አልባ በራሪ ቁስ (ድሮን) እንደሌለ የኢንፎርሜሽን መረበ ደኅንነት ኤጀንሲ አስታወቀ።