
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 03/2013ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ፋንታ ማደፍሮ (ዶክተር) የተመራ የክልሉ የዞን እና የወረዳ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን ደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ 027 ኮትቻ ቀበሌ የበርሃ አንበጣ መከላከል እንቅስቃሴውን ምልከታ አድርገዋል፡፡ በቀበሌው የበረሃ አንበጣው ከተከሰተ ከ20 ቀናት በላይ ቢሆንም አርሶ አደሩ ባደረገው ያላሰለሰ ርብርብ የከፋ ጉዳት አለማድረሱን ተመልክተዋል፡፡
በምሥራቅ አማራ ስለተከሰተው የበርሃ አንበጣ እስካሁን 270 ሺህ ሄክታር መሬት ቅኝት ተካሂዷል፤ በ200 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ አንበጣው መከሰቱ ተረጋግጧል፤ 72 ሺህ ሄክታር መሬቱ ላይ የመከላከል ሥራ ተሠርቷል፤ 30 ሺህ ሄክታር በአውሮፕላን ቀሪው ደግሞ አርሶ አደሩን ያሳተፉና በባህላዊ መንገድ የተካሄደ የመከላከል ሥራ መሆኑ ተገልጿል፡፡ አርሶ አደሮቹ የኬሚካል መርጫ እና ኬሚካል እንዲቀርብላቸው ለሥራ ኃላፊዎቹ ጥያቄ አቅርበዋል። ቀበሌው የመንገድ ችግር ስላለበት ግብዓቱን ለማጓጓዝ አስቸጋሪ እንዳደረገውም አመልክተዋል፡፡ የእርሻ ማሳቸው ከመኖሪያ መንደሮቹ የራቀ ቢሆንም ጊዜያዊ መጠለያ በማዘጋጀት እና አደረጃጀት በመፍጠር ከዚያው እየዋለ እያደረ ሰብሉን ከአንበጣ መንጋው እየተከላከለ ነው ተብሏል፡፡ እናም አንበጣው እንደሌላው አካባቢ በተሁለደሬ ወረዳ 027 ኮትቻ ቀበሌ የከፋ ጉዳት አላደረሰም፡፡ የክልሉ መንግሥት የበርሃ አንበጣውን በመከላከል እና የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ ያላሰለሰ እገዛ እንደሚያደርግ ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው- ከተሁለደሬ
