
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 03/2013ዓ.ም (አብመድ) የኢፌዴሪ የመከላከያ ሠራዊት ማንኛውንም ተልዕኮ ለመፈፀም በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ የመከላከያ ሚኒስትር ቀንዓ ያደታ (ዶክተር) ገለፁ።
ሚኒስትሩ የመከላከያ ሚኒስቴር የ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የሥራ አፈፃፀምን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
‘‘የሠራዊቱ ተቀባይነት እየጨመረ መምጣቱን አረጋግጠናል’’ ያሉት ሚኒስትሩ ገለልተኛ ተቋም መፍጠር መቻሉን አስታውቀዋል።
ሠራዊቱ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆኖ ሕግ መንግሥታዊ መርህን መሠረት በማድረግ ተልዕኮውን እየተወጣ እንደሆነም ገልጸዋል።
የክልሎችን የፀጥታ ግንባታ በተመለከተ ደረጃ ለማዘጋጀት ሥራዎች እየተሠሩ መቆየታቸውን አስታውሰው ከዚህ ጋር ተያይዞም የክልሎች የፀጥታ ግንባታ ለብሐየራዊ አንድነት አደጋ ካላመጣ እና ሰላምና ፀጥታን ለማረጋገጥ እገዛ የሚያደርግ ከሆነ ያን ያክል የጎላ ችግር እንደሌለው አውስተዋል።
ሠራዊቱ ከፌዴራል ፖሊስ እና ከክልል የፀጥታ አካላት ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሠራር ጥሩ እንደሆነ መገምገሙንም ገልፀዋል።
በአቅም ግንባታ ዘርፍም በሦስት ወራቱ የተለያዩ መንግሥት ያስቀመጣቸውን የአቅም ግንባታ ስትራቴጂዎችን መሠረት በማድረግ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውንም ነው ያነሱት።
በዚህም የሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ እና ሌሎችም ተያያዥ ሥራዎች በፍጥነት መሠራታቸውን ጠቅሰዋል።
የቀጣናውን ሰላም በጋራ ለመጠበቅ እና ቀጣናዊ ትብብርን ለማጎልበትም ወታደራዊ ዲፕሎማሲ ሥራ እየተሠራ መሆኑን መግለጻቸውንም ፋብኮ ዘግቧል።
በመተከል ዞን የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ለማስቆምና አካባበውን ወደ ሰላማዊ አንቅስቃሴ ለመመለስ ሠራዊቱ በአካባቢው ከሚገኘው ኮማንድ ፖስት ጋር በሙሉ አቅሙ እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው የፀጥታ ችግር እንዲፈጠር በማድረግ የተጠረጠሩ አካላትም በቁጥጥር ስር ውለው ተጠያቂ እየተደረጉ እንደሚገኙ ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡
ሰሞኑን በአካባቢው የተከሰተው ችግር ምንም እንኳን መነሻው ግለሰባዊ ፀብ ቢሆንም ሠራዊቱ ግን በዚህ ድርጊት የተሳተፉትን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ እና አካባቢው ወደ ቀድሞ ሰላሙ አንዲመለስ የማድረግ ሥራ እየሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
‘‘ከመስከረም 30 በኋላ መንግሥት የለም’’ በሚል ሲነዛ የነበረው ወሬ ኢትዮጵያን በትክክል ካለማወቅና ካለመረዳት የመጣ ተራ ጩኸት መሆኑን በመጥቀስም ‘‘ከመስከረም 30 በኋላ መንግሥት እንዳለ ሀገሪቷም እንዳልፈረሰች እያየን ነው’’ ብለዋል፡፡
