በዓለም የግማሽ ማራቶን የሚሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ዛሬ ይሸኛል፡፡

244

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 03/2013ዓ.ም (አብመድ) በፖላንድ ጊዲኒያ በሚካሄደው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፕዮና የሚሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ዛሬ አሸኛኘት እንደሚደረግለት ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡

አሸኛኘቱን የሚያደርገው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ነው፡፡ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ቅዳሜ ጥቅምት 07 ቀን 2013 ዓ.ም በፖላንድ ጊዲኒያ ለ24ኛ ጊዜ በሚካሄደው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፕዮ ሀገራችውን የሚወክሉ አትሌቶችን ለመምረጥ የማጣሪያ ውድድር በማካሄድ ለአንድ ወር የሚሆን ጊዜ ዝግጅት ማድረጉም ታውቋል፡፡ አትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ማጣሪያውን አልፈው ዝግጅት ሲያደርጉ የነበሩ አትሌቶችን ነው ዛሬ የሚሸኜው፡፡ በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ በሁለቱም ፆታ እንደምትወከል ነው አትሌቲክስ ፌደሬሽኑ በማኅበራዊ ገፁ ያስታወቀው፡፡

በወንድ አትሌቶች ኢትዮጵያን የሚወክሉ ኃይለማርያም ኪሮስ ከበደው፣ አንዱዓምላክ በልሁ በርታ፣ ዓምደወርቅ ዋለልኝ ታደሰ፣ ጉዬ አዶላ ኢዳሞ እና ልዑል ገብረሥላሴ ዓለሜ ናቸው፡፡

በሴቶች ደግሞ ኢትዮጵያን ወክለው በዓለም አቀፉ መድረክ የሚሳተፉት ያለምዘርፍ የኋላው ደንሳ፣ ነፃነት ጉደታ ከበደ፣ ዘይነባ ይመር ወርቁ፣ አባበል የሻነህ ብርሃኔ እና መሠረት ጎላ ሲሳይ እንደሆኑ ታውቋል፡፡

ውድድሩ የፊታችን ቅዳሜ ጥቅምት 07 ቀን 2013 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡ የዓለም ግማሽ ማራቶን ባለፈው መጋቢት እንደሚካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረ ቢሆንም በወቅቱ በአውሮፓ የኮሮናቫይረስ እየተስፋፋ በመምጣቱ ነበር የተራዘመው፡፡

Previous article“ለዜጋው የሚጨነቅና የሚቆረቆር መንግሥት ቀድሞ እርምጃ ይወስዳል፡፡” ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ
Next articleሠራዊቱ ማንኛውንም ተልዕኮ ለመፈፀም በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ የመከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡