
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 03/2013ዓ.ም (አብመድ) በምሥራቅ አማራ የተከሰተውን የበርሃ አንበጣ ለመከላከል ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ያሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ርብርብ እያደረጉ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ የግብርና ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ወንዳለ ሀብታሙ ለአብመድ እንዳሉት ቀደም ሲል ሲያገለግሉ የነበሩ አውሮፕላኖች አንዳንዶቹ ብልሽት አጋጥሟቸዋል፤ ጥቅምት 02/2013 ዓ.ም በአንድ አውሮፕላን አምስት ጊዜ የኬሚካል ርጭት ሲደረግ ዉሏል፡፡ “አሁን የተቸገርነው መንጋው በአንድ አካባቢ ሲጠፋ በሌላ አካባቢ ይታያል፣ መንጋው በሰፊው የሚስተዋልበትን አካባቢ የሚያጠና አንድ ሄሊኮፕተር አለ፤ የርጭት ቅደም ተከተሉ የሚሆነው ደግሞ በመንጋው ስፋት ስለሆነ ስምሪቱ ከምትቃኘው ሄሊኮፕተር በሚገኘው መረጃ መሠረት ነው” ብለዋል ሚንስትር ዴኤታው፡፡ የርጭት ስምሪት የሚሰጠው መንጋው በስፋት ጉዳት ሊያስከትል በሚችልበት ቦታ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
መንግሥት የበርሃ አንበጣን መታገል ከጀመረ ከአምስት አስከ ስድስት ወራት እንደሆነው አቶ ወንዳለ ገልጸዋል፡፡ የመንጋው ስፋት ሊኖር የቻለው ከውጭ ሀገራት በአዲስ መልኩ የሚገባ የአንበጣ መንጋ በመኖሩ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የተከሰተው የበርሃ አንበጣ ለመቆጣጠር እንዲቻል እስከ ጥቅምት 4/2013 ዓ.ም አራት የመርጫ አውሮፕላኖች ከውጭ ወደ ሀገር እንደሚገቡም አስታውቀዋል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው እንደገለጹት አንድ አውሮፕላን በቀን 4 ሺህ ሄክታር ስፋት ያለውን አካባቢ የመርጨት አቅም አለው፤ እናም በቅርቡ የሚጠበቁት አውሮፕላኖች ከተሰማሩ መንጋውን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ይቻላል፡፡
በአማራ ክልል በ125 ቀበሌዎች እና በ4 ዞኖች የበርሃ አንበጣ መንጋ ተከስቷል፡፡ በመንጋው ምክንያት ለተጎዱ አርሶ አደሮች ድጋፍ የማድረስ ሥራ እንደሚሠራ፣ በሁለተኛ ዙርም ቋሚ በሆነ መልኩ ወደ መስኖ ልማት በማስገባት የሚጠናከሩ እንደሆነ ሚንስትር ዴኤታው ጠቁመዋል፡፡ “መንጋውን አሁን ባለበት ቦታ ማስቆም ታላቅ ሥራ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ በመላውን የሀገሪቱ ክፍል ሊያጠፋ ይችላል” ብለዋል አቶ ወንዳለ፡፡ አንበጣውን በመታገል ከአርሶ አደሩ ጋር እየሠሩ መሆናቸውን እና መጥፋቱ አስኪረጋገጥ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ
