“እንደ ሀገር ተመሳሳይ ጉዳት ከደረሰብን በቀላሉ መሻገር ይከብደናልና ቀሪ አቅማችንን አሟጠን መከላከል ሥራ ላይ ልናውል ይገባል፡፡” ምክትል ርእሰ መሥተዳደር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶክተር)

132

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 03/2013ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶክተር) የተመራ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር በበርሃ አንበጣ መንጋ ወረርሽኝ የተጎዱ አካባቢዎችን ተመልክተዋል፡፡

በምሥራቅ አማራ በርካታ አካባቢዎች የበርሃ አንበጣ መንጋ ተከስቶ በሰብል ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት አድርሷል፡፡ የበርሃ አንበጣው ጉዳት ካደረሰባቸው አካባቢዎች አንዱ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ነው፡፡ በብሔረሰብ አስተዳደሩ ካሉት ሰባት ወረዳዎች ውስጥ በአምስቱ ወረዳዎች በሚገኙ 46 ቀበሌዎች ላይ የአንበጣ መንጋው ተከስቶ ጉዳት አድርሷል፡፡ ተዘዋውረን ባየናቸው አንዳንድ አካባቢዎች ከፊል ጉዳት ሲያስከትል በበርካታ ቀበሌዎች ግን ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ በማሳ ላይ የነበረውን ሰብል አውድሟል፡፡

በብሔረሰብ አስተዳደሩ የበርሃ አንበጣ መንጋ መከሰት ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰባቸው ወረዳዎች ውስጥ ባቲ አንዱ ነው፡፡ ወረዳው ካሉት 26 ቀበሌዎች በ21ዱ የአንበጣ መንጋው ተከስቶ ሙሉ በሙሉ በማሳ ላይ ባለ ሰብል ጉዳት አድርሷል፡፡ በዘመናዊ እና ባህላዊ መንገድ ለመከላከል ጥረት ቢደረግም የአንበጣው ሥርጭት ከቁጥጥር ውጭ የሆነባቸው አርሶ አደሮቹ ቢቸግራቸው የማሽላ አገዳቸውን በእራፊ ጨርቅ እስከ መሸፈን ደርሰዋል፡፡

“የምንችለውን ሁሉ አድርገን በመጨረሻም እጅ ሰጥተናል” ያሉት አርሶ አደር ዑመር ሰይድ መንግሥት በአፋጣኝ እንዲደርስላቸውም ጠይቀዋል፡፡ “ችግሩ በእኛው አካባቢ እና አንድ ጊዜ ብቻ ተከስቶ የሚያቆም አይደለም” ያሉት የአካባቢው አርሶ አደሮች የመከላከል ሥራው ከምንጩ እንዲሆንም ተማፅነዋል፡፡

በበርሃ አንበጣ መንጋው ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች ተዘዋውረው የጎበኙት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶክተር) ክስተቱን “ቅስም ሰባሪ” ብለውታል፡፡ ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ የክልሉ እና የፌዴራል መንግሥታት ሁለት ነገሮች ከፊታቸው እንደሚጠብቃቸውም ነግረውናል፤ ለተጎጅዎች አፋጣኝ ድጋፍ ማድረግ እና ችግሩን በዘላቂነት መቆጣጠር፡፡

ጉዳቱ የደረሰባቸው አርሶ አደሮች የዕለት ጉርስ እንደሚያስፈልጋቸው ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ አስታውቀዋል፤ የክልሉ መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሰጥም ጠቁመዋል፡፡ ‘‘የተከሰተው ችግር ከባድ በመሆኑ እንደ ሀገር ተመሳሳይ ጉዳት ከደረሰብን በቀላሉ መሻገር ይከብደናልና፤ ቀሪ አቅማችንን አሟጠን መከላከል ሥራ ላይ ልናውል ይገባል” ብለዋል ዶክተር ፋንታ፡፡

የገጠመንን ችግር ለመሻገር ትርፍ አምራች በሆኑ አካባቢዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል፤ የመከላከል ሥራው አሁንም በተጎዱ አካባቢዎች ጭምር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ የአንበጣ መንጋውን በበቂ ሁኔታ መከላከል ካልተቻለ በመስኖ በሚዘሩ ሰብሎች እና በእንስሳት መኖ ላይም የከፋ ጉዳት እንደሚያደርስ አሳስበዋል፡፡

“ሁሉም አካባቢዎች በበርሃ አንበጣ መንጋው ሙሉ በሙሉ ወድሟል፤ ነገር ግን ወድሟል ብሎ የመከላከሉን ሥራ ማቆም ተገቢ አይደለም፤ ምክንያቱ ችግሩ ሀገራዊ እንዳይሆን እና የበለጠ ዋጋ እንዳያስከፍል አጥብቆ መሥራት ያስፈልጋል” ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -ከባቲ

Previous articleበድጋሜ በኮሮናቫይረስ የተያዘው ሰውየ ከመጀመሪያው የከፋ ሕመም አጋጥሞታል፡፡
Next articleየበርሃ አንበጣ መከላከል ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡