ሐይቁ በመሙላቱ ወደውጭ የተገፋው የእምቦጭ አረም ተመልሶ እንዳይገባ የሰው ኃይል ሊሠማራ ነው፡፡

255

ባሕር ዳር፡ መስከረም 29/2013ዓ.ም (አብመድ) ከጣና ሞልቶ መፍሰስ ጋር ተያይዞ ከሐይቁ የወጣውን እምቦጭ አረምን ለማስቀረት የሰው ኃይል ሊሰማራ መሆኑን የጣና ሐይቅና ሌሎች የውኃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡

ጣና ሐይቅ ሞልቶ መፍሰሱን ተከትሎ የእምቦጭ አረምም ከነባሩ የጣና ሐይቅ ይዞታው ሸሽቷል፡፡ ይህም የእምቦጭ አረምን በመከላከል ሂደቱ እንደ መልካም አጋጣሚ የሚቆጠር መሆኑን ኤጄንሲው ገልጿል፡፡ አረሙ ከሐይቁ መውጣቱ የሰው ኃይልን በመጠቀም ባለበት ለማስቀረት አመቺ በመሆኑ አጋጣሚውን ለመጠቀም እየሠራ መሆኑን ነው ኤጀንሲው ያስታወቀው፡፡

ወደ ማሳ የወጣውን የእምቦጭ አረም ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ከተቻለ ቀጣዩ ሥራ ተንጠባጥቦ የቀረውን መልቀም ነው፡፡ ወደ ማሳ የወጣውን ባለበት ማስቀረት ካልተቻለ ግን በማሳ እና በሐይቁ ውስጥ በፍጥነት እንደሚራባ ተመላክቷል፡፡

በመሆኑም የውኃ መጠኑ በሚቀንስ ጊዜ አረሙ ወደ ሐይቁ ተመልሶ እንዳይገባ ባለበት ለማስቀረት እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ሰው መግባት እስከሚችልባቸው ቦታዎች ድረስ ሥምሪት እንደሚደረግም የኤጄንሲው ሥራ አስኪያጅ አያሌው ወንዴ (ዶክተር) አስታውቀዋል፡፡

በዚህ ጊዜም በፎገራ፣ ሊቦ ከምከም እና ደምቢያ ወረዳዎች በሚገኙ በ30 ቀበሌዎች ሠራተኞችን የሚያስተባብር ሰው የመሟላት ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት፡፡ አስተባባሪዎቹም ከወረዳ እና ከቀበሌ አስተዳዳሪዎች ጋር ወደ ተግባር የሚገቡ ይሆናል፡፡

እንደሥራ አስኪያጁ ገለጻ ጣና ሞልቶ በፈሰሰባቸው አካባቢዎች አረሙን ለማስወገድ በቂ የሰው ኃይል ይገኛል፡፡ መልካም አጋጣሚውን በመጠቀምም በተቻለ ፍጥነት ወደ ተግባር የሚገባ ይሆናል፡፡ እንደ ዶክተር አያሌው ማብራሪያ ሠራተኞቹ አረሙን በመሰብሰብ አንድ ቦታ ያከማቹታል፤ ከተሰበሰበ በኋላም በበጋ ጊዜ የሚቃጠል ይሆናል፡፡

ሐይቁ ሞልቶ ባልፈሰሰባቸው አካባቢዎች ያለውን የእቦጭ አረም በማሽን ለማስወገድ የክልሉ እና የፌዴራል መንግሥታት የተግባር ድርሻ መለየቱንም አስታውቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ ለጉዳዩ እየሰጡት ያለው ምላሽ በችግሩ አሳሳቢነት ልክ አለመሆኑን ተናግረዋል። ኤጂንሲው ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ዛሬ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ውይይት እንደሚያደርግም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ፎቶ፡- ከፋይል

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Previous articleበጓጉሳ ሽኩዳድ ወረዳ 80 ሺህ ሐሰተኛ ብር ተያዘ፡፡
Next articleበኩር ጋዜጣ ጥቅምት 2/2013 ዓ/ም ዕትም