በጎርፍ አደጋ ለተፈናቀሉ ዜጎች 2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደረገ፡፡

101

ባሕር ዳር፡ መስከረም 29/2013ዓ.ም (አብመድ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመራጭ ሴቶች ኮከስ አባላት በሶማሌ ክልል በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የ2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡

የተከሰተው የተፈጥሮ አደጋ መፈናቀልና የንብረት ውድመት ያስከተለ በመሆኑ ኮከሱ ከምክር ቤቱ፣ ከመንግሥት ልማት ድርጅቶችና መሰል ተቋማት ጋር በመሆን የተለያዩ ድጋፎችን ሲያሰባስብ መቆየቱን የሴቶች ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና የኮከሱ ሥራ አስፈጻሚ አበባ የሱፍ ገልጸዋል፡፡

‘‘ምክር ቤቱ የሕዝብ ውክልና ወስዶ የሚሠራ እንደመሆኑ መጠን እንዲህ ዓይነት ችግር በኅብረተሰቡ ዘንድ ሲደርስ ከሕዝብ ጎን መቆም አለበት’’ ያሉት ወይዘሮ አበባ የተደረገውም ድጋፍ የዚሁ ተግባርና ኃላፊነት ማሳያ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ከተከሰተው ችግር አንጻር ሲታይ የተደረገው ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ በተለይ የችግሩ ሰለባ ሴቶችና ሕጻናት በመሆናቸው ክልሉም ትኩረት ሊሰጥበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የኮከሱ አባል ወይዘሮ ፋንታዬ ባቡሎ በበኩላቸው ኮከሱ በሴቶችና ሕጻናት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራ እንደመሆኑ የሴቶች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እና ከተጎጂነት ለማላቀቅ የበኩሉን እንደሚሠራ ነው የተናገሩት፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ምሥራቅ መኮንን (ዶክተር) ደግሞ እንደነዚህ ዓይነት በኅብረተሰቡ ላይ የሚከሰቱ የተለያዩ ችግሮች በምክር ቤቱ የመከታተልና የመቆጣጠር ተግባር ውስጥ የሚካተቱ መሆናቸውን ገልጸዋል፤ የተደረገውን ድጋፍ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ ረገድ የክልሉ መሪዎች ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ኡስማን ፋራ በበክላቸው ክልሉ በየጊዜው ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ከሚከሰቱባቸው አንዱ እንደመሆኑ አሁን ላይ ችግሩን ለመቅረፍ የተባበረ ክንድ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ከምክር ቤቱ በተደረገው ድጋፍ ደስተኛ መሆናቸውንና ለተጎጅዎች ለማድረስም የበኩላቸውን እንደሚወጡም ነው ያስታወቁት፡፡

የምክር ቤቱ ሴቶች ተመራጭ ኮከስ ከዚህ በፊት በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ እና ጋምቤላ ክልሎች በተፈጠሩት አለመረጋጋቶችና በተፈጥሮ አደጋ ከቀያቸው ለተፈኛቀሉትና ጉዳት ለደረሰባቸው ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

Previous articleበመምህርነት ሲያገለግሉ የነበሩ ባለሙያዎች ሀጋራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጅት እንዲያደርጉ ተጠየቀ፡፡
Next articleበኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ባቲ ወረዳ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ አሁን ላይ በብሔረሰብ አስተዳደሩ አምስት ወረዳዎች ላይ እየተስፋፋ መሆኑ ተገለፀ፡፡