
የአንበጣ መንጋዉም በአምስት ወረዳዎች በሚገኙ 46 ቀበሌዎችን የሸፈነ ሲሆን ከ7 ሺህ 200 ሄክታር በላይ ሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ታውቋል። በዚህም ከ12 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የችግሩ ሰለባ መሆናቸዉን የብሔረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ያገኘነዉ መረጃ ያመለክታል፡፡
ለአብነትም በባቲ ወረዳ ብቻ በ15 ቀበሌዎች የሚገኝ ሰብል ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መዉደሙን የብሔረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኃላፊ እብሬ ከበደ ገልፀዋል፡፡
ጉዳቱንም ለመከላከል በባህላዊና በዘመናዊ መንገድ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የገለፁት የመምሪያ ኃላፊዉ በዚህ ተግባር ላይም የመንግሥት ሠራተኞች፣ ባለሀብቶች፣ እንዲሁም አርሶ አደሮች እየተሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አቶ እብሬ ከበደ አክለዉም አሁን ላይ በአንድ አዉሮፕላን የኬሚካል ርጭት እየተደረገ መሆኑን በመግለፅ ከችግሩ በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ከ7 እስከ 10 አዉሮፕላን እንደሚያስፈልግ በባለሙያ የተጠና መሆኑን ገልፀዋል። የክልሉ ግብርና ቢሮና የፌዴራል የግብርና ሚኒስቴር ጉዳዩ ጊዜ የማይሰጥ መሆኑን ከግምት ዉስጥ በማስገባት በጋራ መፍትሔ ሊያበጁለት እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ይማም ኢብራሂም -ከከሚሴ