
ኅብረተሰቡም ከፖሊስ ጋር በቅንጅት እንዲሠራ ጥሪ ቀርቧል፡፡
በኢትዮጵያ አዳዲስ የብር ኖቶች መቀየራቸውን ተከትሎ ሐሰተኛ የብር ኖቶች እየተበራከቱ ነው፡፡ አዳዲስ የብር ኖቶችንና ነባሮቹን የብር ኖቶች በማስመሰል ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላት በየቦታው መያዛቸውም እየተዘገበ ነው፡፡ በአማራ ክልልም በተለያዩ አካባቢዎች ሐሰተኛ የብር ኖቶች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው፡፡ ኅብረተሰቡን ከሐሰተኛ የብር ኖት ለመጠበቅና ኪሳራ እንዳይገጥመው በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
የኮሚሽኑ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር መሠረት ደባልቄ ለአብመድ እንዳሉት ሐሰተኛ የብር ኖቶች በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ሲዘዋወሩ እየተገኙ ነው፡፡ ፖሊስም በክትትል በቁጥጥር ስር እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የክልሉ ፖሊስ የምርምራ ቡድን በሁሉም አካባቢዎች እንቅሰቃሴ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ሐሰተኛ የብር ኖቶችን ይዘው የሚገኙ ሰዎችን ወደ ሕግ እያቀረበ በሕግ እርምጃ እንዲወሰድባቸው እያደረገ ነውም ብለዋል፡፡በምርመራ ላይ ያሉ መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡ ፖሊስ ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን ኮማንደር መሠረት ተናግረው ኅበረተሰቡም ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሐሰተኛ የብር ኖቶችን ዋነኛ ምንጭ ለመለየትም ፖሊስ በምርመራ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በተለይም በቀበሌና በወረዳ ገበያዎች ላይ እየገቡ አርሶ አደሩን ለማሳሳት ጥረት የሚያደርጉ አካላት መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡ በገበያና በባንክ ላይ እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎችን የፀጥታ ኃይሉ በጥብቅ እየተከታተለ መሆኑን አስታውቀዋል። የባንክ አገልግሎት በማያገኙ አካባቢዎች ኅብረተሰቡን ከሐሰተኛ የብር ኖት ለመጠበቅ በተለየ ቁጥጥር እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ እስካሁን ሐሰተኛ የብር ኖት ይዘው በተገኙ ላይም እርምጃ የተወሰደባቸው ያሉ መሆናቸውን ነው ኮማንደር መሠረት የተናገሩት፡፡ ኅብረተሰቡ የሐሰተኛ የብር ኖቶችን ለመከላከልና ለኪሰራ እንዳይደረግ ግብይቱን በባንክ ማድረግ እንደሚገባውም ኮማንደር መሠረት አሳስበዋል፡፡ የባንክ አገልግሎት በማይገኝባቸው አካባቢዎችም በተለየ ጥንቃቄ መገበያየት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
ስለ ትክክለኛ የብር ኖቶች መለያ ምልክቶች በሚገባ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሠራት እንዳለበትም ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡ ችግሩን ለመከላከል ፖሊስ በሚያደርገው ጥረት ኅብረተሰቡ እንደተለመደው በቅንጅት እንዲሠራም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ