የሰቆጣ ቃል ኪዳን በ2022ዓ.ም የሕጻናት መቀንጨርን ዜሮ ለማድረግ ጠንክሮ እንደሚሠራ አስታወቀ፡፡

316

የሰቆጣ ቃል ኪዳን የመንግሥትመረ ቃል ኪዳን መሆኑን የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ፈንታ ማንደፍሮ (ዶክተር) ገልጸዋል፡፡

እንደፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ የሰቆጣ ቃል ኪዳን በ2012 በጀት ዓመት ነፍሰ ጡር እናቶች፣ የሚያጠቡ እናቶችና ከአምስት ዓመት በታች የሆኑትን ሕጻናት የጤናና ሥርዓተ ምግብ ተጠቃሚ በማድረግ ሲሠራ ቆይቷል፡፡

ባለፈው በጀት ዓመት የሰቆጣ ቃል ኪዳን፣ በአማራና ትግራይ ክልሎች የሚገኙ 40 ወረዳዎች ማኅበረሰብን ደግፏል፤ ከፌዴራል መንግሥት እና ከሁለቱ ክልሎች በተገኘ 893 ሚሊዮን ብር ድጋፉ ሲካሄድ እንደነበር በጤና ሚኒስቴር የእናቶች እና ሕጻናት ዳይሬክተር መሠረት ዘላለም (ዶክተር) አስረድተዋል፡፡ የፕሮጀክቱ 2012 በጀት ዓመት ሪፖርት እና 2013 በጀት ዓመት እቅድ ትውውቅ መድረክ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ ላይ ዳይሬክተሯ እንዳብራሩት ባለፈው በጀት ዓመት የሰቆጣ ቃል ኪዳን የእቅዱን 72 ነጥብ 5 በመቶ ነፍሰ ጡር፣ የሚያጠቡ እናቶችንና ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናትን የጤናና ሥርዓተ ምገባ ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ የእቅዱን 73 ነጥብ 8 በመቶ በንጥረ ነገር የበለጸጉ ምግቦች ተደራሽ አድርጓል፤ የዕቅዱን 74 ነጥብ 2 ከመቶ ሰዎችን የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ ማድረግም ችሏል፡፡

የሰቆጣ ቃል ኪዳን በ40 ወረዳዎች የትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ማስወገድ ንቅናቄ በማድረግ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሲፈታ እንደቆየም ዶክተር መሠረት ገልጸዋል፡፡

“በ2013 በጀት ዓመት ከባለፈው አፈጻጸም ትምህርት በመውሰድ፣ ከነበረው ደካማ ጎን በመማር፣ ችግሮች በጋራ የሚፈቱበት መንገድ ተለይቷል፡፡ በዚህ ዓመት ከፌዴራልና ከክልል መንግሥታት የተመደበውን 331 ሚሊዮን ብር በፍጥነት ወደ ሥራ የሚገባበት መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል” ብለዋል ዳይሬክተሯ፡፡ ሁሉንም ያሳተፈ ርብርብ በማድረግ መቀንጨርን ዜሮ ለማድረግ የሚደረገው እንቅስቃሴ ከግብ እንደሚደርስ እምነታቸው እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡

በሰቆጣ ቃል ኪዳን የርእሰ መሥተዳድሩ አማካሪ ዓለሙ ጀምበር የአማራን ክልል ሕዝብ የመልማት ጥያቄዎች በይደር በማቆየት የሚሸሽበት ዕድል እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ “በመቀንጨር የተነሳ ውድ የሆነ ሀብታችንን ነው እያጣን ያለነው፤ በተለይ በተከዜ ተፋሰስ ችግሩ የሰፋ በመሆኑ አመራሩ፣ ማኅበረሰቡ እና አሁን ያለው ትውልድ ርብርብ ማድረግ ያለበት አሁን ነው፡፡ ቃል ኪዳናችን ሥርዓተ ምግብን ማሻሻል የእድገታችን ማዕከል እናድርግ” ብለዋል አማካሪው፡፡

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር ፈንታ ማንደፍሮ (ዶክተር) የሰቆጣ ቃል ኪዳን የመንግሥትም ቃል ኪዳን እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ ለፕሮግራሙ ማስፈጸሚያ በ2013 በጀት ዓመት ከፌዴራል መንግሥት 331 ሚሊዮን 200 ሺህ ብር፣ ከክልል መንግሥት 220 ሚሊዮን 404 ሺህ 795 ብር በመመደብ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ዶክተር ፈንታ አስረድተዋል፡፡ የሰቆጣ ቃል ኪዳን በ2022 ዓ.ም የሕጻናት መቀንጨርን ዜሮ ለማድረግ አልሞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ሥርዓተ ምግብን ለማሻሻል የኅብረተሰቡን ግንዛቤ እና ገቢ መጨመር ለእቅዱ መሳካት ወሳኝ መሆኑንም ነው ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ የጠቆሙት፡፡

ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Previous articleየጎንደርና ባሕር ዳር ዩንቨርሲቲዎችን ጨምሮ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ልህቀት ማዕከል ተብለው ተለዩ።
Next articleበመምህርነት ሲያገለግሉ የነበሩ ባለሙያዎች ሀጋራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጅት እንዲያደርጉ ተጠየቀ፡፡