የጎንደርና ባሕር ዳር ዩንቨርሲቲዎችን ጨምሮ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ልህቀት ማዕከል ተብለው ተለዩ።

267

በኢትዮጵያ ስምንት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ልህቀት ማዕከል በመባል መለየታቸውን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች በትምህርት ጥራት ዙሪያ ያካሄደውን የምርምር ግኝቶች ላይ ትናንት ከባለድርሻዎች ጋር ተወያይቶል።

የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ወርቁ ነጋሽ እንደገለጹት በሀገሪቱ የሚገኙ 46 ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በአጠቃላይ ትምህርት በሚል በሦስት ደረጃዎች ተለይተዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በርካታ ችግር ፈቺ የምርምር ውጤቶችን ሲያበረክቱ የቆዩና ወደፊትም አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል የተባሉ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር ዘርፍ የልህቀት ማዕከል እንዲሆኑ መለየታቸውን ተናግረዋል፡፡

“ጎንደር፣ አዲስ አበባ፣ ባሕር ዳር፣ መቀሌ፣ ጅማ፣ ሐዋሳ፣ አርባምንጭና ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ልህቀት ማዕከል እንዲሆኑ ተለይተዋል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት እንደዘገበው ለአንድ ሀገር ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ችግር ፈቺ ምርምር ቁልፍ ሚና እንዳለው የገለጹት ዶክተር ወርቁ “ያደጉ ሀገሮች የእድገት ሚስጥርም ከዚህ የመነጨ ነው” ብለዋል፡፡

የምርምር ዩኒቨርሲቲዎቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር አቻ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አቅማቸውን ለመገንባት በትኩረት እንደሚሠራ አመላክተዋል፡፡

ሌሎች 15 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትምህርትና ስልጠና እንዲሰጡ መለየታቸውን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲዎቹ በቂ ዕውቀትና ክህሎት ያዳበረ ዜጋ ማፍራት እንዲችሉ ተከታታይ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አመላክተዋል።

ቀሪዎቹ 23 ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ አጠቃላይ ትምህርትና ስልጠና እንዲሰጡ የተለዩ መሆኑን ዶክተር ወርቁ አስታውቀዋል ።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት መርሻ ጫኔ (ፕሮፌሰር) ዩኒቨርሲቲው በርካታ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Previous articleጥንቅሽ ቁረጡ እና ምጠጡ!
Next articleየሰቆጣ ቃል ኪዳን በ2022ዓ.ም የሕጻናት መቀንጨርን ዜሮ ለማድረግ ጠንክሮ እንደሚሠራ አስታወቀ፡፡