
ባሕር ዳር፡ መስከረም 29/2013ዓ.ም (አብመድ) ሞት አሳዛኝ ዑደት ነው፤ ተስፋ አስቆራጭ ሲሆን ግን አስተውለን አናውቅም፡፡ ቋሚ አልቅሶ ሟችን እስከወዲኛው ይሸኛል፤ ሕይወት ግን ነገም በሌላ ምዕራፍ እና በተተኪ ትውልድ ትቀጥላለች፡፡ ሞት ዑደት እንጂ ክስተት አይደለምና ከድንጋጤ እና ሐዘን በዘለለ ተስፋ አስቆራጭ ሆኖ አያቅም፤ ቢያውቅ እንኳን በተቀባዩ ጥንካሬ እና ድክመት የሚወሰን ነው፡፡ እንዲህ መሰል ተስፋ አስቆራጭ ክስተት ሲያጋጥም ደግሞ መፈጠራችን እስክንረግም ድረስ ነገሮች አስቀያሚ መልክ ይኖራቸዋል፡፡ ተፈጥሮን ታግሎ የሚኖር ጠንካራ አርሶ አደር ተስፋ ቆርጦ ስታይ ደግሞ የስቃዩ ስሜት የከፋ ነው፡፡
በዚህ አካባቢ መኖር በራሱ የነዋሪዎቹን አሸናፊነት ይመሰክራል፡፡ ከዳሎል የሚመጣው ወበቅ ያቃጥላል፡፡ አካባቢው ከአፈር ይልቅ እንደ ጅብራ የተገተረ አለት እና ጠጠር ይበዛዋል፡፡ በአካባቢው አረፍ ብሎ ቀልብን ለመግዛት ከግራር ዛፍ ጥላ የተሻለ ነገር የለም፡፡ የሰው ልጅ እስከኖረበት ድረስ ስያሜው ተገቢ አይደለም ካልተባለ በስተቀር ለአካባቢው ‹ምድረ በዳ› ከሚል ስያሜ የተሻለ መጠሪያ ማግኘት ይከብዳል፡፡
ከሀራ ገበያ ዘጠኝ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ወደ አፋር ክልል ሲጓዙ ትንሽየ መንደር ያገኛሉ፤ ሀሮ፡፡ ሀሮ ነዋሪዎቿ ለመንደሯ የሰጧት መጠሪያ ነው፡፡ የረጃጂም ማሽላ ማሳ ውዝዋዜ አልፎ አልፎ ከሚስተዋለው የነጭ ጤፍ ስስ ዘለላ መዘናፈል ጋር ተዳምረው ለአካባቢው ሙቀት መጠነኛ ነፋሻማ አየር ለግሰውታል፡፡ ከላይ የሚመጣው የፀሐይ ሙቀት ያለከልካይ ምድሪቱን ያቃጥላታል፡፡
ወደ አካባቢው ስንደርስ የሰማነው ድምፅ ውስጥን ይረብሻል፡፡ “የእህል ያለሽ” የሚለው ዘለግ ያለው የልመና ድምፅ ከሕጻናት እስከ አዛውንት፣ ከሴት እስከ ወንድ እና ከሊቅ እስከ ደቂቅ ይሰማል፡፡ ጠጠር የገባባቸው የውኃ መያዣ ላስቲኮች ድምፅ፣ የጎማ ጭስ፣ የብረት ምጣድ ቋቋታታ፣ ጡሩምባ እና ድምፅ ማጉያ ከዚህኛው ተራራ እስከ አሻጋሪው ኮረብታ አብዝቶ ይሰማል፡፡ ሄሊኮፕተር ከሰማይ ጄኔሬተር በምድር የሚረጩት ኬሚካል በአካባቢው ያለውን አየር አብዝቶ ለውጦታል፡፡
ይህ ሁሉ ባህላዊ እና ዘመናዊ ርብርብ በአካባቢው የተከሰተውን የበርሃ አንበጣ መንጋ ውድመት ለመቀነስ ነበር፡፡ ግን ይህ ሁሉ ውጣ ውረድ የተሳካ አይመስልም፤ በሁለት ሰዓታት ልዩነት ያረፈበትን ሁሉ ዱቄት እያደረገ ይርመሰመሳል፡፡ ሲቀሰቅሱት ይነሳል፤ ነገር ግን ርቆ አይሄድም፡፡ ከአንዱ ግራር ተነስቶ ወደ ሌላው ማሳ ያርፋል፡፡ ከተነሳበት ቦታ ግን መልሶ ሲያርፍ አይስተዋልም፤ ምን ቀርቶት ይመለሳል?
“ድሮ ድሮ እኛ ልጅ እያለን የአባቶቻችን ስጋት ነበር” ያሉን የ80 ዓመታት አዛውንቱ ሸህ ሁሴን በልጅነታቸው አንድ ጊዜ የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ ተከስቶ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ከዚያ ውጭ ግን የበርሃ አንበጣ ከስጋት ያለፈ ጥቃት ሲያስተውሉ ዛሬ በእስተርጅና ዘመናቸው መሆኑ ነው፡፡
ከማሽላ ዘለላ ራስ ላይ የሚርመሰመሰውን የአንበጣ መንጋ እያዩ ዐይናቸው እምባ ያቀረረው ሸህ ሁሴን “ሻሽ ትመስላለች” ከሚሏት ጤፍ ማሳ ዳር ተቀምጠው ለበቅ ያወዛውዛሉ፡፡ “አካል እንጂ ልብ እኮ አያረጅም” እጃቸው እስኪዝል እያንፏቀቁ በአካባቢው የሰፈረውን አንበጣ ሲቀሰቅሱ ጠጋ ብየ አነጋገርኳቸው፡፡ “አሏህ ያመጣውን በላ አሏህ እስኪመልሰው፤ አላሃምዱሊላሂ እንጂ ሌላ ምን ይባላል” ያሉኝ ሸህ ሁሴን ወፍ ሲጮህ መጥተው እንደተቀመጡ ናቸው፡፡ ከቤታቸው በታች ያለ የልጆቻቸው ማሳ ትናንት እንዳይሆን ሆኗል፤ ዛሬ ደግሞ ቀሪ ያሉትን ተነጥቀው ዘመንን በምልሰት ከወጣትነት እስከ ሽምግልና በትዝብት አሰናስለው ቡዝዝ ባሉ እና ቅራኔ ባዘሉ ዐይኖቿቸው የመጣውን በፀጋ ይሸኙታል፡፡
በሌሎች አካባቢዎችም ተመሳሳይ አሳዛኝ ክስተቶች ይስተዋላሉ፡፡ በርካቶቹ ከማሽላ ማሳቸው ዳር ተቀምጠው መጪውን በተስፋ መቁረጥ ይጠብቃሉ፡፡ ከ10 ቀናት በላይ በመሰል ተግባር ተጠምደው ቆይተዋል፡፡ ብቸኝነት በቀያቸው ባይተዋር አድርጓቸዋል፡፡ ማንንም አይወቅሱም፣ ማንንም አይነቅሱም ለጠየቃቸው ሁሉ “አሏህ ያመጣውን በላ አሏህ እስኪመልሰው” የሚል ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ እንደዛም ሆኖ ግን እጆቻቸውን አጣጥፈው ለብዙ ጊዜ የሚጠብቁም አይደሉም፤ ተነስተው “የእህል ያለሽ” ይላሉ የያዙትን ነገር እያስጮሁ፡፡
ቢያንስ ለከብት መኖ ቢሆን ብለው ከተበላው ማሽላ ስር ያለውን አገዳ ይቆርጣሉ፡፡ አንጀት በሚበላ እና ማንነታቸውን በሚያጎላ ድምፅት ያዩትን እንግዳ ሰው ሁሉ ደግሞ “ጥንቅሽ ቁረጡ እና ምጠጡ” ሲሉ መስማት እንዴት እንደሚረብሽ ለማየት እንደ እኛ በቦታው መገኘትን ይጠይቃል፡፡
እነርሱ ፈጣሪ የሰጣቸውን በፀጋ ተቀብለው ፈተናውን ሁሉ በሚችሉት ሊያሳልፉ ደፋ ቀና ይላሉ፤ ነገር ግን ችግሩ አፋጣኝ ምላሽ ካልተሰጠው ከአካባቢው አልፎ እንደሚዛመት እና የከፋ ጉዳት እንደሚያደርስ ለመናገር የግድ ነብይ መሆንን አይጠይቅም፡፡ “የመንግሥት ያለሽ” ጎልቶ ሊሰማ የሚገባ የአካባቢው ጥሪ ነው፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m