የኮሮናቫይረስ ስርጭት እየጨመረ ሲሄድ በተቃራኒው የሚጓዘው የማኅበረሰቡ መዘናጋት እንዳሳሰበው የክልሉ ጤሮ ቢሮ አስታወቀ።

178

ባሕር ዳር፡ መስከረም 29/2013ዓ.ም (ባሕር ዳር) የኮሮናቫይረስ ከጊዜ ወደ ጊዜ ስርጭቱ እየጨመረ ቢሄድም ማኅበረሰቡ እራሱን ከኮሮናቫይረስ እየጠበቀ አለመሆኑን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታውቋል።

የኮሮናቫይረስ እስካሁን ድረስ መድኃኒት ወይም ክትባት ያልተገኘለት ወረርሽኝ ነው። በመሆኑም በሽታውን ለመከላከል አራቱ የ”መ” ሕጎች ማለትም (መቀመጥ፣ መታጠብ፣ መጠቀም እና መራራቅ) ተግባራዊ ሲደረጉ ቆይተዋል። ነገር ግን በሀገራችን ተጥሎ የነበረው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳቱን ተከትሎ ኅብረተሰቡ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ሲለብስ፣ እጁን በእግባቡ ሲታጠብ፣ እንዲሁም አካላዊ ርቀቱን ሲጠብቅ አይስተዋልም።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮም በቀጣይ ትምህርት ቤቶች ሲከፈቱ የበሽታው ስርጭት እንዳይስፋፋ እና ኅብረተሰቡ የሚያሳየው መዘናጋት የወረርሽኙን ስርጭት እንዳያባብሰው የሃይማኖት አባቶች ለኅብረተሰቡ አሁንም ማስተማር እንዳለባቸው አሳስቧል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ከሁሉም ዞኖች ከተውጣጡ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር ውይይት አካሂዷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች እና ከኅብረተሰቡ ውስጥም “ኮሮና የለም፣ ለፖለቲካ ማስፈፀሚያ ነው” የሚሉ የተሳሳቱ አመለካከቶች መኖራቸው ስርጭቱ እንዲስፋፋ አድርጎታል ብለዋል። በቀጣይም ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር በኩል የሃይማኖት አባቶች ያላሳለሰ ጥረት በማድረግ ኃላፊነታቸውን መውጣት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

የጤና ባለሙያዎች እና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የመከላከያ መንገዶችን በመተግበር አርዓያ ሊሆኑ እንደሚገባም የሃይማኖት አባቶች መክረዋል።

“ኅብረተሰቡ ‘ኮሮና የለም’ ከሚል አስተሳሰብ ወጥቶ እራሱን እና ወገኑን ሊጠብቅ ይገባል” ያሉት የሃይማኖት አባቶች መንግሥትም ሕግን በማስከበር በኩል ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ አማረ ሊቁ – ከደብረታቦር

Previous articleበሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ የተከሰተው የበርሃ አንበጣ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ መምጣቱን የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
Next articleሥርዓትን ሳይሆን ሕዝብን ማገልገል የሚችል፣ ዘመናዊና ዘመን ተሻጋሪ ፖሊስን መገንባት የሚያስችል የኢፌዴሪ ፖሊስ ዶክተትሪን ይፋ ተደረገ።