
ባሕር ዳር፡ መስከረም 29/2013ዓ.ም (አብመድ) የአግልግሎት ዘርፍ ኢንቨስትመንቱ ግን ዝቅተኛ መሆኑን የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር አስታውቋል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ቢሆንም የአገልግሎት ዘርፉ ገና ያልተነካ መሆኑን የከተማዋ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡
ከኢንቨስትመንቱ መስፋፋት በተጨማሪም ከተማዋ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገች እንደሆነ ተገልጿል፡፡ የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ብርሃን ገብረሕይወት እንዳሉት በደብረ ብርሃን ከተማ 198 ሆቴሎች እና ቅይጥ ሕንጻዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል አንድ የባለ አንድ እና አንድ የባለሁለት ኮከብ ደረጃ ያላቸው ናቸው፡፡የአገልግሎት ዘርፉ እድገት ከአምራች ዘርፉ እና ከከተማው እድገት ጋር ባለመመጣጠኑ ለመስተንግዶ አዳጋች መሆኑንም ኃላፊው ጠቅሰዋል።
አካባቢው የቱሪዝም መዳረሻ ነው፡፡ የገጠር ወረዳዎች ምቹ የሆቴል እና ቱሪዝም አገልግሎት ባለመስጠታቸው ጎብኝዎች ደብረ ብርሃን እንዲያርፉ ይገደዳሉ፡፡ በሌላ በኩል ከተማዋ ለአዲስ አበባ ቅርብ በመሆኗ የኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻ እንድሆን ያስችላታል፡፡ የኢንቨስትመንቱ መስፋፋት ከከተማዋ ፈጣን እድገት ጋር ተዳምሮ ለአገልግሎት ዘርፉ አዋጪነት መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡ ይሁን እንጂ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑን አቶ ብርሃን ተናግረዋል፡፡
እንደ ኢንዱስትሪው ለአገልግሎት ዘርፉ ከተማው በራሱ መንገድ ፈቃድ መስጠት የሚያስችል መመሪያ አለመኖሩ ለችግሩ እንደምክንያት ተነስቷል፡፡ ምንም እንኳን የዘርፉ ኢንቨስትመንት አናሳ ቢሆንም የፈቃድ አሰጣጡ የተወሳሰበ መሆን ለኢንቨስትመንት ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ የአገልግሎት ዘርፍ የኢንቨስትመንት ጥያቄ ሲቀርብ ከተማው ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ በዞኑ በኩል ለክልል ቀርቦ ነው ምደባ የሚደረገው፡፡
በዚህ መሠረት 13 የተለያየ የኮከብ ደረጀ ያላቸው ሆቴሎች እንዲሠሩ ተመድቧል፡፡ ከነዚህ መካከል ወደ ግንባታ የገቡት አምስቱ ብቻ ናቸው፡፡ በቅረቡም ተጨማሪ 14 የሪል ስቴት እና የኮከብ ደረጃ ያላቸው ሆቴሎች ጥያቄን ለመመለስ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ በዞኑ በኩል ለክልል መንግሥት ለማሳወቅም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ጽሕፈት ቤት ኃላፊው ዘርፉን ለማነቃቃት እና ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የሆቴል፣ የሎጂ እና የመዝናኛ ቦታዎችን በመለየት ለባለሀብቶች በጨረታ ለማስተላለፍ ተግራዊ እንቅስቃሴ እንደተጀመረም አስታውቀዋል፡፡ በዚህም ከ5 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ መሬት በማዘጋጀት ለሦስት ባለሀብቶች በሊዝ ተላልፏል፡፡ የሚፈለገውን ደረጃ ባያሟሉም በርከት ያሉ ባለሀብቶች በየግላቸው ቦታ ገዝተው ሆቴሎችን እየገነቡ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
የከተማዋ እድገት በመፍጠኑ ለ10 ዓመታ የተዘጋጀው የከተማ ልማት ፕላን በአራት ዓመቱ መሙላቱም በኢንቨስትመንቱ ላይ ያጋጠመ ችግር ነው፡፡ ክልሉ ለኢንዱስትሪ ዘርፉ 2 ሺህ 500 ሄክታር ማስፋፊያ ቦታ መጨመሩን ተናግረዋል፡፡ የአገልግሎት ዘርፉ እንዲስፋፋም የከተማዋን እድገት ታሳቢ ያደረገ መፍትሔ ለመስጠት እየተሠራ እንደሆነም አመላክተዋል፡፡ ደብረብርሃን ከተማን ወደ ሪጂዎፖሊታን ለማሳደግ የተጀመረው እንቅስቃሴም ይህንን ለማስተካከል እንደሚረዳ ነው አቶ ብርሃን ያስታወቁት፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ