በሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ የተከሰተው የበርሃ አንበጣ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ መምጣቱን የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

379

ባሕር ዳር፡ መስከረም 29/2013ዓ.ም (አብመድ) በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮችም ‹‹ጉዳቱ በእኛው ያቁም፤ ባልተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚደረገው የመከላከል ሥራ ይጠናከር›› ብለዋል፡፡ ድጋፍ ከተደረገ እንኳን ሰብሉ ሙሉ በሙሉ ቢወድምም ለእንስሳት መኖ እንዲተርፍ የደረሰም ያልደረሰም ሰብል በመሰብሰቡ እገዛ እንዲደረግላቸው እየተማፀኑ ነው፡፡

ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በምሥራቅ አማራ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው የበርሃ አንበጣ መንጋ ለአካባቢው አርሶ አደሮች ስጋት ሆኖ ነበር፡፡ በያዝነው አዲስ ዓመት መስከረም 6 ቀን 2012 ዓ.ም አካባቢ በምሥራቁ የአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች የተከሰተው የበርሃ አንበጣ መንጋ ግን እንዳለፈው ዓመት ስጋት ሆኖ የሚያልፍ አልሆነም፡፡ ከተዘራው ሰብል አልፎ ለከብቶች መኖ የሚሆነው አገዳም በአንበጣ መንጋው እየወደመ ነው፡፡

አቶ ኑሬሁሴን ሐሰን በሀብሩ ወረዳ 27 ቀበሌ የሚኖሩ አርሶ አደር ናቸው፡፡ ገና በፈጂር ወደሀራ ገበያ አቅንተው 10 የቀን ሠራተኞችን ለእያንዳንዳቸው በ200 ብር ሒሳብ አምጥተው በማሳቸው አሰማርተዋል፡፡ ‹‹የእህል ያለሽ›› የሚለው የአቶ ኑሬሁሴን ድምፅ የአንበጣ መንጋውን ከማሽላ ማሳው የሚያስነሱበት ብቻ ሳይሆን ፈጣሪን የሚለምኑበትም ይመስላል፡፡ ከአንደኛው የማሳው ጫፍ ያየናቸው አቶ ኑርሁሴን በፍጥነት ሌላኛው የማሳው ጫፍ ላይ ሲራወጡ ሲታዩ አንጀት ያላውሳሉ፡፡

ቤተሰቦቻቸው ሌላ ማሳ ላይ ተሰማርተው እንደ ሸማኔ መወርወሪያ ከወዲያ ወዲህ መካለብ ከጀመሩ 11 ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ ‹‹በአካባቢው ተወልጀ ሳድግ አባቶቻችን ከሚያወሩት በዘለለ መሰል አደጋ አይቸ አላውቅም›› ያሉን አርሶ አደሩ ተስፋ መቁረጥ ከፊታቸው ላይ ይነበባል፡፡ ‹‹ዛሬ ግን አውቄዋለሁ እጅ ሰጥተናል፤ ላልደረሰባቸው አካባቢዎች እንዳይተርፍ ነው ልፋታችን›› ብለዋል በተስፋ መቁረጥ፡፡

በምድር እና በሰማይ የኬሚካል ርጭት፣ የየሰፈሩ ጭስ እና ጩኽት መንጋውን ከሰብላቸው ነቅነቅ አላደርገው ያለ መሰል አርሶ አደሮች በተስፋ መቁረጥ የደረሰውንም ያልደረሰውንም ሰብል ቆረጣ ላይ ናቸው፡፡ የልዩ ኃይሎች አስለቃሽ ጭስ፣ የከባድ ተሸከርካሪዎች ጡሩምባ፣ የአውሮፕላን ኬሚካል ርጭት ያልረታው የበርሃ አንበጣው መንጋ አረንጓዴ ዛፍ ላይ ሰፍሮ ላየው አበባ ይመስላል፡፡ ነገር ግን ከሰዓታት ቆይታ በኋላ መንጋው ካረፈበት ግራር ላይ ሲነሳ ዛፉ ችራሮ እንጨቱ ቀርቶ ይታያል፡፡

በቦታው ያገኘናቸው የሀብሩ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተመቸ ሲሳይ ችግሩ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ መምጣቱን ነግረውናል፡፡ 39 የገጠር ቀበሌ ባላት ሀብሩ ወረዳ 13ቱ ቀበሌዎች ላይ የበረሃ አንበጣ መንጋው ተከስቷል፡፡ አንድ ቀበሌ ላይ የተዘራ ሰብል ሙሉ በሙሉ ሲወድም ቀሪ 12ቱ ቀበሌዎች እስከ 95 በመቶ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

“በ13ቱ ቀበሌዎች 7 ሺህ 965 ሄክታር መሬት በሰብል ተሸፍኖ ነበር” ብለዋል የግብርና ጽፈሕት ቤት ኃላፊው፤ በ6 ሺህ 650 ሄክታር መሬት ሰብል ላይ የበርሃ አንበጣው አርፎ 5 ሺህ 270 ሄክታሩን ሙሉ በሙሉ እንዳወደመም ነግረውናል፡፡ በእነዚህ ቀበሌዎች የበርሃ አንበጣው ስርጭት ከቁጥጥር ውጪ በመሆኑ አሁን ሌሎች ቀበሌዎችን እና አዋሳኝ ወረዳዎችን እንዳያጠቃ የመከላከል ሥራ ላይ መሆናቸውንም ነግረውናል፡፡ የአውሮፕላን ኬሚካል ርጭቱ ለውጥ የሚያመጣ ቢሆንም የመልክአ ምድራዊ አቀማመጡ፣ ሰዎችና እንስሳት በአካባቢው መኖራቸው እና አንድ ሄሊኮፕተር ብቻ በመኖሯ አሷን በተራ ለመጠቀም መገደዳቸው የመከላከል ሥራውን ሳንካ እንደፈጠረበት ተናግረዋል አቶ ተመቸ፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው- ከሰሜን ወሎ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleበበረሃ አንበጣ መንጋ በሰብላቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ነዋሪዎች እንዲደገፉ ተጠየቀ፡፡
Next articleየከተማዋ ዕድገት በመፍጠኑ ለ10 ዓመት የተዘጋጀው ፕላን በአራት ዓመት ተጠናቅቋል፡፡