በበረሃ አንበጣ መንጋ በሰብላቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ነዋሪዎች እንዲደገፉ ተጠየቀ፡፡

403

ባሕር ዳር፡ መስከረም 28/2013ዓ.ም (አብመድ) በደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በ11 ቀበሌዎች በሚገኝ ሰብል ላይ ሙሉ በሙሉ ጉዳት ማድረሱን ተከትሎ ለኅብረተሰቡ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን በወረባቦ ወረዳ የበረሃ አንበጣ መንጋ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎችም የአንበጣ መንጋው የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ በባህላዊ መንገድ ጭስ በማጨስና፣ ጅራፍ በማጮህ ለመከላከል ጥረት ቢያደርጉም ከአቅም በላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከባህላዊ መከላከያ መንገዶች ባሻገር በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት ቢደረግም የበረሃ አንበጣ መንጋውን መቆጣጠር እንዳልተቻለ ነው የተናገሩት፡፡

አሁን ላይ ሰብሉ ገና ያልደረሰና በእሸት ደረጃ ላይ በመሆኑ ቀድመው ለመሰብሰብ አለመቻላቸውንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ ‘‘እስከዛሬ የምንችለውን ሁሉ አድርገናል፤ አሁን ላይ ጉዳቱን ከመመልከት ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም፡፡ መንግሥት አስፈላጊውን እገዛ ያድርግልን’’ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የወረባቦ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ሙዓዝ ሙሀመድ እንደገለጹት የበረሃ አንበጣ መንጋው በወረዳው 11 ቀበሌዎች የሚገኝ ሰብል ላይ ሙሉ በሙሉ ጉዳት አድርሷል፡፡ በሌሎች ሦስት ቀበሌዎች ደግሞ በከፊል ጉዳት ማድረሱን አስታውቀዋል፡፡

የመንጋው ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ ስጋቱ አሁንም ከፍተኛ እንደሆነም አቶ ሙዓዝ አመልክተዋል፡፡ የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት ውጤታማ ቢሆንም አውሮፕላኑ አንድ ብቻ መሆኑ ውጤታማ እንዳላደረገው ገልጸዋል፡፡

ሰብላቸው የወደመባቸውን አርሶ አደሮችን መንግሥትና ኅብረተሰቡ ድጋፍ ሊያደርግላቸው እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
የአንበጣ መንጋው ወደሌሎች አዋሳኝ ወረዳዎች እየሄደ በመሆኑ የፌዴራል መንግሥት ተጨማሪ የኬሚካል መርጫ አውሮፕላኖችን እንዲያሰማራም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ተመሥገን አሰፋ -ከወረባቦ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም (አብቁተ) ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክት 20 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ፡፡
Next articleበሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ የተከሰተው የበርሃ አንበጣ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ መምጣቱን የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡