
ባሕር ዳር፡ መስከረም 28/2013ዓ.ም (አብመድ) በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እና በጎርፍ አደጋ እየተፈተነ ያለው የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የበርሃ አንበጣ መንጋም የራስ ምታት ሆኖበታል፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ የበርሃ አንበጣ መቆጣጠሪያና መከላከያ ድርጅትን ጨምሮ የሀገራቱ መንግሥታት ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የመከላከል ሥራ እየሠሩ ቢሆንም አሁንም መንጋውን ለመግታት ያላሰለሰ ጥረት ይጠይቃል ተብሏል፡፡
የአንበጣ መንጋው በርሃማ ከሆኑ የቀጣናው አካባቢዎች መነሻውን ቢያደርግም ወደ አማራ ክልል ከፍተኛ ቦታዎች እና ወደ ሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ስርጭቱን ሊያሰፋ እንደሚችል የምሥራቅ አፍሪካ የበርሃ አንበጣ መቆጣጠሪያና መከላከያ ድርጅት አሳስቧል፡፡ በድርጅቱ የመረጃና ትንበያ ከፍተኛ ባለሙያ ፈለገ ኤልያስ ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በሰጡት መረጃ አንበጣው እርጥበታማ እና አረንጓዴ የሆኑ አካባቢዎችን ይመርጣል፤ በቆላማ አካባቢዎች የሙቀት መጠኑ እየጨመረ ስለሚሄድና አረንጓዴ ቅጠሎች እና ሰብሎች ስለሚደርቁ ምቹ ወደሆኑ የአማራ ክልል ከፍተኛ ቦታዎች ብሎም ወደ ሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍሎች ሊስፋፋ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የበርሃ አንበጣ መንጋው በተከሰተባቸው አካባቢዎች ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ርብርብ እየተደረገ እንደሆነም ባለሙያው ገልጸዋል፡፡ የአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት ማካሄድ ወሳኝ መፍትሔ በመሆኑ የመከላከል ሥራውን ለማገዝ የሚረዳ በድርጅቱ አንድ አውሮፕላን የፊታችን ቅዳሜ ኢትዮጵያ እንደሚገባም አስታቀዋል፡፡
አውሮፕላኑ በዩጋንዳ የበረሃ አንበጣ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የኬሚካል ርጭት ሲያካሂድ እንደነበር ባለሙያው ገልጸው እዛ አካባቢ ያለው ስርጭት በመሻሻሉ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት መወሰናቸውን ነግረውናል፡፡
አውሮፕላኞችን ከሌሎች መከላከያና መቆጣጠሪያ መንገዶች ጋር መጠቀም ከተቻለ ችግሩን መቅረፍ እንደሚቻል አቶ ፈለገ ተናግረዋል፡፡ የበርሃ አንበጣውን ለመከላከል የቀጣናው ሀገራት ቅንጅታዊ ጥረት እንዲያደርጉ እየሠራ መሆኑንም ድርጅቱ አስታውቋል፡፡
የበርሃ አንበጣውን ከፀረ ተባይ ኬሚካል ለየት ባለ መልኩ መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ጥናትና ምርምር እየተካሄደ እንደሆነ ከምሥራቅ አፍሪካ የበርሃ አንበጣ መቆጣጠሪያና መከላከያ ድርጅት ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡
ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m