
ባሕር ዳር፡ መስከረም 28/2013ዓ.ም (አብመድ) ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የትግራይ ብሔር ተወላጆች ከባሕር ዳር ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።
ውይይቱ ስለኢሕአዴግ ውሕደት፣ ስለውህደቱ አስፈላጊነት፣ የህወኃት ከውሕደቱ ስለማፈንገጥ፣ የብልፅግና ፓርቲ ዓላማ እና እሴቶች እንዲሁም የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። የውይይቱ ተሳታፊ አቶ መብራህቱ ሐዱሽ “በርካታ የትግራይ ተወላጆች ሀብት እና ንብረት ያፈራነው ትግራይ በመሆን አይደለም፤ ወንድም ከሆነው የአማራ እና ኢትዮጵያዊ ሕዝብ ጋር ሆነን ነው፤ አሁን ደግሞ በትግራይ ክልል ከሚገኙ ዘመዶች ጋር ስልክ እንኳን ደውለን ስለ ወቅቱ የፖለቲካ ሁኔታ ለማውራት አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሯል፤ ይህ ደግሞ ለዘመናት ለተሠራው ኢትዮጵዊነት ትልቅ እንቅፋት ነው” ብለዋል፡፡
በተለይም የህወኃት ባለስልጣናት የስልጣን ጥማታቸውን ለማርካት ሲሉ ለዘመናት አብሮ የኖረውን ሕዝብ ከመለያየት እና ታሪካዊ ስህተት ከመሥራት ሊቆጠቡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ሐጎስ ፀሐይ በባሕር ዳር ከተማ 40 ዓመታት እንደኖሩና ትግሬ በመሆናቸው አንድም ተፅዕኖ ደርሶባቸው እንደማያዉቅ ተናግረዋል፡፡ “መንግሥት አሁንም ቢሆን ከህወኃት ባለስልጣናት ጋር የተካረሩ ጉዳዮችን በውይይት መፍታት ቢችል መልካም ነው” ሲሉም አስተያዬት ሰጥተዋል፡፡
ተሳታፊዎቹ የህወኃት ባለሰልጣናት ከዚህ በፊት የተለያዩ ታርጋዎችን በመለጠፍ በሕዝብ ላይ የፈጸሙት በደል ዘግናኝ እንደነበር አንስተዋል፡፡ ከዚህ ችግር ለመውጣት ብልፅግና ፓርቲ ኅብረ ብሔራዊነትን በማጠናከር ወደ ፊት መጓዝ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተመሥገን በላቸው የአማራ እና የትግራይ ሕዝቦች የፖለቲካ ሴራ የሚነጣጥላቸው እንዳልሆኑ ገልጸዋል፡፡ በታሪክም የአማራ እና ትግራይ ሕዝቦች ሀገር በመገንባት እንጂ ሀገር በማፍርስ እንደማይታወቁም ተናግረዋል፡፡ አሁን ከህወኃት የሚታየው ጊዜያዊ ማፈንገጥም በሁለቱ ሕዝቦች ጠንካራ ኢትዮጵያዊነትን ለመገንባት የሚደረገውን ጉዞ እንደማያደናቅፍም ገልጸዋል፡፡ ባሕር ዳር ከተማ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆችም ለለውጡ ከፍተኛ አስተዋፆ ማድረግ እንዳለባቸውም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ብልፅግና ፓርቲም ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር ሁሉንም ሕዝቦች በእኩል ለማገልገል ቁርጠኛ መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴክተር ተቋማት ማስተባበሪያ ዘርፍ ኃላፊ ሀብቶም ገብረእግዚአብሔር ደግሞ ህወሀት ከዚህ በፊት የውሕደቱን ፅንሰ ሐሳብ በመረዳት እና ወደ ውሕደቱ ለመምጣት ዋና አቀንቃኝ እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን አብዮታዊ ዲሞክራሲ ፅንሰ ሐሳብን በውሕደቱም ማስቀጠል ስለሚፈልጉ ወደ ውሕደቱ ለመምጣት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፤ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ስህተቶችን ማስተካከል የማይቻለውና እየፈረጀ ስለሚሄድ ወቅቱን የሚመጥን ጉዞ ለማድረግ እንደማያስችልም አስገንዝበዋል፡፡ በተቃራኒው ብልፅግና በኅብረ ብሔራዊነት መልካም ነገሮችን በማስቀጠል እና ስህተቶችን በማረም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚኖርባት የጋራ ሀገር ለመገንባት እንደሚያስችል አቶ ሀብቶም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሺባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m