
ባሕር ዳር፡ መስከረም 28/2013ዓ.ም (አብመድ) በሰሜን ሸዋ ዞን አራት ወረዳዎች የበረሃ አንበጣ መንጋ ተከስቷል፡፡ በቀወት ወረዳ እምባይ ጎድ ሙቅ ውኃ በሚባል አካባቢ 16 ሄክታር መሬት ላይ የአበረሃ አንበጣ መንጋ ተከስቷል፡፡
የተከተሰውን የበረሃ አንበጣ መንጋ ለመከላከልም ከሌሊት አስር ሰዓት ጀምሮ የአካባቢው አርሶ አደሮች፣ የመንግሥት ሠራተኞችና የአማራ ክልል የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት ጥረት እያደረጉ ውለዋል፡፡ የቀወት ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ታደሰ ማሙሸት የበረሃ አንበጣ መንጋው በባሕሪው ተንቀሳቃሽ በመሆኑ በዘመናዊ መንገድ የሚደረገውን የመከላከል ሥራ ፈታኝ እንዳደረገባቸው አስታውቀዋል፡፡ አርሶ አደሮቹም የበረሃ አንበጣ መንጋውን ለመከላከል በባህላዊ መንገድ ጅራፍ በማስጮህ፣ ከፍተኛ የሆነ ድምፅ በማውጣት፣ በጭስና በተለያዩ አማራጮች ለመከላከል ጥረት እያደረጉ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ መሠረት ኃይሌ በአውሮፕላን ርጭት ለማካሄድ ሸዋ ሮቢት የሚገኜውን የአውሮፕላን ማረፊያ የማፅዳትና ሥራ እንደሚሠራና ወደ እርጭት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል የአንበጣ መንጋ መከላከል ግብረ ኃይል መቋቋሙንም መምሪያ ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡ ግብረ ኃይሉም የበረሃ አንበጣ መንጋውን ለመከላከል የሚያስችሉ ነገሮችን እያዘጋጀ እንደሆነ ወይዘሮ መሠረት ገልጸዋል፡፡
በዞኑ አራት ወረዳዎች ላይ የበረሃ አንበጣ ተከለስቷል ነው የተባለው፡፡ የበረሃ አንበጣ የተከሰተባቸው ወረዳዎች ምንጃር ሸንኮራ፣ በረኸት፣ቀወትና አሳግርት ናቸው፡፡ የበረሃ አንበጣው በአፋር ክልል ኩማሜ ወረዳ እንደሚነሳም ተገልጿል፡፡ የበረሃ አንበጣውን በጋራ ለመከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከአፋር ክልል ጋር መረጃ እየተለዋወጡ እንደሆነም የዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡
ወረርሽኙን ለመከላከል በሚደረገው ሥራ አርሶ አደሩ ተሳታፊ እንዲሆንም ጥሪ ቀርቧል፡፡ የበረሃ አንጣ መንጋው በዞኑ እስካሁን ድረስ በሰብል ላይ ጉዳት አለማድረሱም ተመላክቷል፡፡
ዘጋቢ፡- ሀብታሙ ዳኛቸው
ፎቶ፡- ቀወት ወረዳ ኮሙዩኒኬሽን
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m