
ባሕር ዳር፡ መስከረም 28/2013ዓ.ም (አብመድ) በጠለምት ወረዳ የባንክ አገልግሎት ባለመኖሩ የብር ኖቱን ለመቀየር መቸገራቸውን የወረዳው ነዋሪዎች ቅሬታ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ እስከትናንት ድረስ አዲሱ የብር ኖት ወደ ወረዳው አለመግባቱ ስጋት እንደፈጠረባቸው ነዋሪዎቹ ለአብመድ ገልጸዋል፡፡
የአማራ ብድር እና ቁጠባ ተቋም (አብቁተ) በጠለምት ወረዳ ቅርንጫፍ ያለው ብቸኛው የፋይናንስ ተቋም ነው፡፡ ታዲያ አብቁተ አዲሱ የብር ኖት ቅያሬን አስመልክቶ ምን እየሠራ እንደሚገኝ አብመድ ጠይቋል፡፡ የአማራ ብድር እና ቁጠባ ተቋም የገበያ እና ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አያልነህ ምሕረቱ እንደነገሩን የመሠረተ ልማት ችግር ባለባቸው እና ባንክ በሌለባቸው ወረዳዎች የአብቁተ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
በክልሉ ባንክ በሌለባቸው እንደ ሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምትና መሰል ወረዳዎች ብሔራዊ ባንክ የሚያሠራጨውን አዲሱን የብር ኖት አብቁተ የመቀየር ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል፤ እስከትናንት ድረስ ርቀት አካባቢ ባሉ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች አዲሱ የብር ኖት ባለመድረሱ በቁጠባ የተሰበሰበውን ብር መቀየር አልተቻለም፡፡ በእነዚህ ወረዳዎች አዲሶቹን የብር ኖቶች በሄሊኮፕተር ጭምር ለአብቁተ ቅርንጫፎች አቅርቦ የብር ቅያሬ እንዲከናወን ከብሔራዊ ባንክ ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን አቶ አያልነህ ገልጸዋል፡፡
ከ100 ሺህ እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚቀይሩ ሰዎችም ቀነ ገደቡ ከመድረሱ በፊት በተቋሙ ሒሳብ ቁጥር ወከፍተው ማስገባት እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡ ብሔራዊ ባንክ የሚያወጣቸውን መመሪያዎች እና የብር ቅያሬ አስመልክቶ በቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በኩል ለማኅበረሰቡ የግንዛቤ ፈጠራ እየተሠራ እንደሆነም አቶ አያልነህ ነግረውናል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m