በመተከል ዞን በተለያዩ ወረዳዎች እየተንቀሳቀሱ ሽብር ሲፈጥሩ በነበሩ 14 የጥፋት ኃይሎች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገለጸ፡፡

410

ባሕር ዳር፡ መስከረም 28/2013ዓ.ም (አብመድ) ከሰሞኑ በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ጉብላክ ቀበሌ በንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃት ካደረሱ ኃይሎች መካከል 14 ያህሉ የተደመሰሱ ሲሆን 2 ደግሞ ከእነ ሙሉ ትጥቃቸው መያዛቸውን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ጋሹ ዱጋዝ ተናግረዋል።

በተወሰደው እርምጃም 5 የክላሽ የጦር መሳሪያዎች እና 10 ኋላ ቀር መሳሪያዎች ጭምር ተይዘዋል።

ከሁለት ቀን በፊት በዳንጉር ወረዳ ጉብላክ ቀበሌ 14 ንጹሃን ዜጎች በአጥፊዎች የተገደሉ ሲሆን ስምንት ደግሞ ቆስለው የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኙ ኃላፊው ግለጻቸውን የመተከል ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

የጥቃቱ ሰለባ ከሆኑት ንጹሃን ሰዎች መካከል አንደኛው የውጭ ሀገር ዜጋ መሆኑን አቶ ጋሹ ዱጋዝ ገልጸዋል።

በዞኑ ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ በመንቀሳቀስ ቀጣናውን ለማዋከ በሚንቀሳቀሱ የጥፋት ኃይሎች ላይ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ በጋራ በመሥራት የሕግ የበላይነትን የማስከበር ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑን ኃላፊ ገልጸዋል።

ቀጣናውን ከጠላት ነፃ ለማድረግ በዞኑ ውስጥ ተደጋጋሚ ግጭት በሚስተዋልባቸው ዳንጉር እና ጉባ ወረዳዎች ውስጥ በተለይ ገጠር አካባቢ የሚኖረው አርሶ አደር ለግብርናም ሆነ በማናቸውም ጉዳዮች እንዳይንቀሳቀስና ላልተወሰነ ጊዜ ባለበት ማዕከል ተረጋግቶ እንዲቆይ አቅጣጫ ተቀምጧልም ነው የተባለው።

የአካባቢውን ሰላም ለማስከበር እና የሕግ የበላይነትን ለማስፈን ከግልገል በለስ ከተማ ወደ ዳንጉርና ጉባ ወረዳዊች የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት እንዳይደረስ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ጨምሮ በሁሉም የፀጥታ አካላት አማካኝነት በማጀብ እየተሠራ እንደሆነም ተገልጿል።

የዞኑን ሰላም በዘላቂነት ለመፍታት የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት የሕዝቡን ደኅንነት ለማስጠበቅ ጸረ ሰላም ኃይሎችን በመደምሰስም ሆነ ወደ ሕግ ለማቅረብ በኩል ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የቢሮ ኃላፊው መግለጻቸውን የመተከል ዞን የመንግሥት ኮሙዩኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዘግቧል።

በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎች በተለያዩ ጊዜ ተፈናቅለው የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ሰብዓዊ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ ወደ ነበሩት ቀየ የማስመለስ ሥራዎችም እየተሠሩ እንደሆነም ተጠቁሟል።

የክልሉ መንግሥት በዞኑ ውስጥ በተደጋጋሚ በሚስተዋለው ግጭት ላይ ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ እና በቸልተኝነት በተመለከቱ በ45 የሥራ ኃላፊዎች ከኃላፊነት እንደተነሱና 15ቱም ጉዳያቸው በሕግ እየታየ እንደሚገኝ ይታወሳል።

የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው የቅድመ ወንጀል መከላከል ሥራ ኅብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመተባበር የበኩሉን አስተዋጽዖ እንዲወጣ ቢሮ ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባው የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
Next article297 ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ ዐረቢያ ተመለሱ፡፡