
ባሕር ዳር፡ መስከረም 28/2013ዓ.ም (አብመድ) በክልሉ አደገኛ መጤ አረሞች በሰብል እና በግጦሽ ቦታዎች ላይ ጉዳት እያስከተሉ እንደሚገኙ የአማራ ክልል የዕፅዋት፣ ዘር እና ሌሎች የግብርና ግብዓቶች ጥራት ቁጥጥር ኳራንታይን ባለስልጣን ገልጧል፡፡
ለእንቦጭ አረም የተሰጠው ትኩረት ለሌሎች አደገኛ መጤ አረሞች ትኩረት ካልተሰጣቸው የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ሊፈተን እንደሚችል የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አሳስቧል፡፡ በወቅቱ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር እየተባለ ይጠራ የነበረው ተቋም በ2010 ዓ.ም ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው አደገኛ እና መጤ አረሞች ከ1970 ዓ.ም ጀምሮ ከተለያዩ ሀገራት ከዕርዳታ እህል፣ ከውጭ በሚገቡ የማሽነሪ ዕቃዎች ጋር እና በሌሎች ምክንያቶች ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል፡፡ በተለምዶ አቅልጥ፣ አቀንጭራ፣ ቅንጬ፣ እምቦጭ፣ የወፍ ቆሎ፣ ሰርክ አበባ፣ አሜኬላ፣ ነጭ ለባሽ እና መሰል አረሞች በሰብል ምርት ላይ ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ። አረሞቹ ብዛት ያለው ዘር የሚያፈሩና በአጭር ጊዜ አካባቢን የመውረር ባሕሪ ያላቸው በመሆናቸው በግብርናው ዘርፍ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደሩ ነው፡፡
እምቦጭን ጨምሮ ብዙዎቹ አረሞች ከደቡብ እና ሰሜን አሜሪካ ሀገራት እንደመጡም ይነገራል። እነዚህ አረሞች 30 በመቶ የሰብል ምርታማነትን የሚቀንሱ ሲሆን የግጦሽ ሳርን ደግሞ ሙሉ በሙሉ የማጥፋት ባሕሪ ያላቸው ናቸው። እንደ ግብርና ሚኒስቴር መረጃ መጤ አረሞቹ በመንገድ ዳር፣ በማሳ ውስጥ፣ በውኃ አካላት ላይ እና በግጦሽ መሬት ላይ የሚበቅሉ ተብለው ተለይተዋል፡፡
የአማራ ክልል የዕፅዋት፣ ዘር እና ሌሎች የግብርና ግብዓቶች ጥራት ቁጥጥር ኳራንታይን ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሙሉጌታ ደባሱ እንደገለጹት በአማራ ክልል 12 ዓይነት አደገኛ እና መጤ አረሞች ይገኛሉ፤ አረሞቹ በአካባቢ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ናቸው፤ እነዚህ አደገኛ መጤ አረሞች ክትትል እና ቁጥጥር ካልተደረገባቸው በአማካይ ከ30 በመቶ በላይ የምርት መቀነስ ያስከትላሉ፡፡ በጣም አደገኛ የሚባሉት አረሞች ደግሞ በቆሎ እና ማሽላ ሰብሎች ላይ ሙሉ በሙሉ ጉዳት የሚያስከትሉ መሆናቸውን አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡
በዚህ ወቅትም በክልሉ 740 ሺህ ሄክታር የእርሻ እና የወል መሬት በአደገኛ እና መጤ አረም መወረሩን ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡ የወረራ መጠኑ ይለያይ እንጅ በክልሉ ከአደገኛ እና መጤ አረም ነፃ የሆነ ወረዳ አለመኖሩን አቶ ሙሉጌታ ነግረውናል፡፡ በተለይም ደግሞ የክልሉ ምሥራቃዊ ክፍል “የወፍ ቆሎ” እየተባለ በሚጠራው አደገኛ መጤ አረም በከፍተኛ ሁኔታ ተወርሯል፡፡ አረሞች በራሳቸው ከሚስፋፉት በላይ በተጎዱ የወል ቦታዎች ላይም ለተፈጥሮ ሀብት ሥራ እንዲውሉ መደረጉ ለመስፋፋታቸው ሌላኛው ችግር ሆኗል፡፡ በክልሉ ለዘር ብዜት አመች የሆኑ ቦታዎች ጭምር በአደገኛ እና መጤ አረም የተወረሩ መሆናቸው ለዘር ብዜትም እንቅፋት መሆኑን ነው ሥራ አስኪያጁ የገለጹት፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጁ መረጃ በተለይ ከፍተኛ ምርት ማምረት በሚያስችሉ እንደብር ሸለቆ ያሉ አካባቢዎች በቅንጨ እና አቀንጭራ አደገኛ መጤ አረሞች በክፍተኛ ሁኔታ ተወርረዋል፤ በዚህም ምክንያት አካባቢው የዘር ብዜት እንዳይካሄድ ታግዷል፤ ሰሜን ጎንደርም “ቦረን” በሚባለው አደገኛ መጤ አረም ተወርሯል፤ የአረሞቹ ዘር ለበርካታ ዓመታት ተቀብሮ የሚቆይ እና ምቹ ሁኔታ ሲያገኝ ተመልሶ የሚበቅል በመሆኑ ለመስፋፋቱ እንደ ምክንያት ተቀምጧል፡፡ አረሞቹ ራሳቸውን በማግዘፍ በሌላ ብዝኃ ሕይወት ላይ ጉዳት እያደረሱ እንደሆነም ተገልጧል፡፡
እስከዚህ ወቅትም በአረሙ አደገኛነት ላይ የክልሉ መንግሥት ትኩረት አለመስጠቱ የመከላከል እና መቆጣጠር ሥራውን አስቸጋሪ አድርጎት መቆየቱን አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡ ለአረሙ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ካልተቻለ ነፃ የሆነ ቦታ በክልሉ ማግኘት እንደሚያስቸግር ነግረውናል፡፡ ይህም በግብርና ምርቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል ተብሏል፡፡ አረሙ በዚህ ወቅት እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለማወቅ የሚያስችል ጥናት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር እየተጠና እንደሚገኝ ዋና ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል፡፡ የጥናቱን ውጤትም በዚህ ዓመት በማጠናቀቅ ለክልሉ የሥራ ኃላፊዎች እንደሚቀርብ ተገልጧል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ኤርሚያስ አባተ (ዶክተር) እንዳሉት ኢንስቲትዩቱ ካለው አቅም ችግር አኳያ አረሞችን ለመቆጣጠር የሚያሥችሉ ቴክኖሎጅዎችን በበቂ ሁኔታ መሥራት አልተቻለም፤ ይሁን እንጅ ባለው አቅም ልክ በኢንስቲትዩቱ የወጡ ምክረ ሐሳቦችን እና ቴክኖሎጅዎችን ጥቅም ላይ አለመዋላቸውም ተጨማሪ ችግር ነው፡፡ አረሞቹ የአፈር ለምነትን በመቀነስ፣ የግጦሽ መሬቶችን በመሸፈንና የውኃ አካላትን በማድረቅ ጉዳታቸው የሰፋ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡ አርሶ አደሮች፣ የግልና የመንግሥት ተቋማት እና ሌሎች አካላት በያዙት መሬት ላይ የተከሰተን አረም እንዴት ማስወገድ እንዳለባቸው የሚያስረዳ የሕግ ማዕቀፍ መቀመጥ እንዳለበት ዶክተር ኤርሚያስ አስገንዝበዋል፡፡
የክልሉ ብሎም የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ምስሶ የሆነው ግብርና ከኋላቀር አስተራረስ እና ከግብዓት አጠቃቀም ችግሮች ባሻገር በአደገኛ እና መጤ አረም እየተፈተነ ይገኛል፡፡ በአካባቢው የሰው ጉልበት በቀላል መንገድ መቆጣጠር እየተቻለ በክልሉ ትኩረት ማነስ አረሙ ዓድማሱን እያሰፋ እንደሚገኝ በሥራ ኃላፊዎቹ ተገልጧል፡፡ አረሞቹ ከክልል ክልል በቀላሉ የሚሰራጩ በመሆናቸው በቅንጅት ሊሠራ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m