
ለመቆጣጠር ሥራው ስምንት የኬሚካል ርጭት የሚያደርጉ አውሮፕላኖች ወደ ሀገር ውስጥ ይገባሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡
ባሕር ዳር፡ መስከረም 27/2013ዓ.ም (አብመድ) የበረሃ አንበጣ መንጋው ባለባቸው አካባቢዎች ጉዳዩን የክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊዎች እንዲመሩት፣ ምክትል ቢሮ ኃላፊዎች በግንባር መስክ ላይ ተገኝተው እንዲሠሩ፣ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታዎች አንድ አንድ ክልል ይዘው እንዲሠሩ እየተደረገ መሆኑን በግብርና ሚኒስቴር ግብርና ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶክተር) አስታውቀዋል፡፡
ለአብነት በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በኃላፊነት ደረጃ ያሉት በክልሉ በአራት ቀጣና (ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ሰሜን ሸዋ) በሥራቸው የሚሠሩ ቴክኒክ ቡድን በማቀፍ የበርሃ አንበጣ መንጋውን ለመከላከልና መቆጣጠር እንዲንቀሳቀሱ ተደርጓል፡፡
የበርሃ አንበጣ መንጋው ዳግም ባየለበት በዚህ ወቅት 112 ተሽከርካሪዎች በአንበጣ ቁጥጥር ሥራ ላይ መሰማራታቸውን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡ “ከዚህ በፊት ስድስት አውሮፕላኖች ነበሩ፡፡ አሁን ላይ ግን ሁለቱ ብቻ ከችግር ነፃ ሆነው አገልግሎት መስጠት ይችላሉ፡፡ አንዷ አውሮፕላን ሰሜን ወሎ ወረባቦ አካባቢ ተከስክሳለች፤ ሌላኛዋ ተበላሽታ ሰመራ ቆማ ትገኛለች፤ ሌሎች ሁለቱ ለጥገና ወደ ኬንያና ደቡብ አፍሪካ ተልከዋል’’ ነው ያሉት፡፡ አውሮፕላኖቹ ተጠግነው እስኪመለሱ ድረስ በሺዎች የሚጠጋ ሄክታር ማሳ ሰብል በአንበጣዎቹ እንዳይበላም ስጋት አለ፡፡
‘‘በመቆጣጠሩ በኩል አቅም መዳከም የተስተዋለው በአውሮፕላኖቹ ቁጥር ማነስ ነው” ሲሉ ዶክተር ማንደፍሮ አብራርተዋል፡፡ በሰው ኃይል፣ በኬሚካል ርጭት፣ በአደረጃጀትና በተሽከርካሪ በመታገዝ ለመቆጣጠር ርብርብ እየተደረገ ስለመሆኑም ነግረውናል፡፡ ይህ ግን በቂ እንዳልሆነና በተለይ የሚበርረውን አንበጣ ለማጥፋት አውሮፕላኖች አስፈላጊ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡
እንደ ዶክተር ማንደፍሮ ገለጻ ኮምቦልቻ ላይ መዳረሻውን ያደረገ አውሮፕላን አሁንም በሥራ ላይ ነው፤ ነገር ግን በአካባቢው አራት ዞኖች የበርሃ አንበጣ መንጋው ተስተውሏል፤ ይህም ከአውሮፕላኑ አቅም በላይ ነው፡፡ በመፍትሔነትም ስምንት ተጨማሪ አውሮፕላኖችን በኪራይ ለማስመጣት ረጅም ሂደት እንደተጓዙ ዶክተር ማንደፍሮ አሳውቀዋል፡፡ ከደቡብ አፍሪካ፣ ሱዳንና ሌሎች ሀገራት አውሮፕላኖቹን በኪራይ ለማስመጣት ጥረቱ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ገልጸዋል፡፡ አውሮፕላኖቹ ከተገኙ የበርሃ አንበጣውን መቆጣጠር እንደሚቻል ዶክተር ማንደፍሮ አረጋግጠዋል፡፡
ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ አውሮፕላኖቹ ኢትዮጵያ እንደሚደርሱ ሚኒስቴር ዴኤታው ጠቁመዋል፡፡ በጣም የከፋ የበረሃ አንበጣ መንጋ በተስተዋለበት አካባቢ በ15 ቀናት ውስጥ ማጥፋት እንደሚቻል አስገንዝበዋል፡፡ ሰብል ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት በእጅጉ መቀነስ እንደሚቻልም አስታውቀዋል፡፡
ከግብርና ሚኒስቴር ውጭ ያሉ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ሁለት ሁለት ተሽከርካሪ አበርክተው በየክልሉ እንዲሰማሩ መደረጉም ተጠቅሷል፡፡ መርጫ መሣሪያና ኬሚካል አቅርቦት ላይም በየክልሉ ማስቀመጥ መቻሉን ሚኒስተር ዴኤታው አመላክተዋል፡፡ ለአብነትም በአማራ ክልል ኮምቦልቻ ላይ 35 ሺህ ሊትር የሚጠጋ ኬሚካል መድኃኒት ዝግጁ ተደርጓል፡፡ በአማራ ክልል በፌዴራል የተመደቡ 17 ተሽከርካሪዎች አሉ፤ ይህም ሆኖ ግን አቅምና ችግሩ ሊመጣጠን እንዳልቻለ ገልጸዋል፡፡ ቀደም ሲል የተከሰተው የበረሃ አንበጣ መንጋ ሊጠፋ በተቃረበበት ወቅት ከሶማሊያ፣ የመንና ጅቡቲ በአዲስ የሚመጣው የበርሃ አንበጣ ችግር መደቀኑን ዶክተር ማንደፍሮ ተናግረዋል፡፡ ትናንት መስከረም 26/2013 ዓ.ም ከሶማሊያ የመጣው የበርሃ አንበጣ ምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌንና ገዋሌን አቋርጦ ወደ ሰሜን ሸዋ እንደገባ ተናግረዋል፡፡
አንበጣው ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በሳር ላይ እንዳለና ወደ ሰብል በሰፊው እንዳልገባ ዶክተር ማንደፍሮ አስረድተዋል፡፡ ከቀበሌ ጀምሮ ከግብርና ሙያ ውጭ ያሉ አካላትን አጠቃሎ በትብብር መሥራት ካልተቻለ ችግሩ ከዚህ የከፋ እንደሚሆንም አሳስበዋል፡፡
የአፍሪካ ቀንድ ጎረቤት ሀገራት ጋር የቅንጅት ሥራው በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) በኩል የሚከወን እንደሆነ ዶክተር ማንደፍሮ አሳውቀዋል፡፡ ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ በኢትዮጵያ የክልል መንግሥታት በጠንካራ ግንኙነት ላይ የተመሠረተ መተባበር እንደሚያስፈልጋቸውም አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m