የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ተሸጠ፡፡

166

ባሕር ዳር፡ መስከረም 27/2013ዓ.ም (አብመድ) የኢትዮጵያ የወንዶች ፕሪሚዬር ሊግ ውድድር የቀጥታ ቴሌቭዥን ስርጭት እና የውድድር ስያሜ መሸጡ ታውቋል፡፡ ውድድሩና ስያሜው የተሸጠው በ22 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ሸር ካምፓኒ የፕሪሚዬር ሊግ ውድድሩን በቀጥታ ቴሌቪዥን ስርጭት ለማስተላለፍ ፍላጎት ያላቸውን ለማሳተፍ ጨረታ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ ሸር ካምፓኒው ባወጣው ጨረታ የተሳተፉ ድርጅቶችን ሲያወዳድርም ቆይቷል፡፡

በተደረገው ውድድርም መልቲ ቾይዝ ኢትዮጵያ ባቀረበው ቴክኒካል እና ፋይናንሻል ፕሮፖዛል የተሻለ ሆኖ በመገኘቱ አሸናፊ መሆኑ ታውቋል፡፡ ድርጅቱ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድርን በዲ ኤስ ቲቪ ለማስተላለፍ ተመራጭ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ድርጅቱ ውድድሩን በቀጥታ ለማስተላለፍ እና ለውድድር ስያሜ ለ5 ዓመታት 22 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪ ዶላር ማቅረቡም ተገልጧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለስልጠና፣ ለአቅም ግንባታ፣ ለፕሮዳክሽን፣ ለአየር ሰዓት ወጪ እና ለአይ ሲ ቲ መሠረተ ልማት ግንባታ ከ45 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንደሚያደርግ ታውቋል፡፡ ድርጅቱ በአጠቃላይ በአምስት ዓመታት ውስጥ “ከ68 ሚሊዮን የአሜሪ ዶላር በላይ ኢንቨስት አደርጋለሁ” ብሏል ነው የተባለው፡፡

ድርጅቱ በተለይም የሀገሪቱን ስፖርት ደረጃ ለማሻሻል በታዳጊ ወጣቶች ላይ፣ የዳኞች እና አሠልጣኞች አቅም ግንባታ፣ ከስታዲም አካባቢ ፀጥታ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው ታውቋል፡፡

ከኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን የተገኜው መረጃ እንደሚያመላክተው ድርጅቱ በአጭር ቀናት ውስጥ ከሊግ ካምፓኒው ጋር የውል ስምምነት በማድረግ ወደ ሥራ እንደሚገባ ሊግ ካምፓኒው አስታውቋል፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleበኢትዮጵያ እየተስፋፋ እና ጉዳት እያደረሰ ያለውን የበርሃ አንበጣ መንጋ ለመቆጣጠር ጠንካራ ርብርብ እያደረገ መሆኑን የፌዴራል ግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
Next articleለተሰንበት ግደይ በ5 ሺህ ሜትር አዲስ ክብረ ወሰን አስመዘገበች።