በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር በተያዘው በጀት ዓመት ከ280 ሺህ በላይ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር እየተሠራ ነው፡፡

160

ያለዋስትና የተሰጠን ብድር ማስመለስ ፈተና መሆኑም ተገልጿል፡፡

ባሕር ዳር፡ መስከረም 27/2013ዓ.ም (አብመድ) ለሥራ እድል ፈጠራው ብድር የሚያቀርበው የአዲስ ብድርና ቁጠባ ከዚህ በፊት ለወጣቶች ያለዋስትና የተሰጠው 2 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድን ማስመለስ ፈተና እንደሆነበት አስታውቋል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ የ2013 በጀት ዓመት የሥራ እድል ፈጠራ ዙሪያ ከባድርሻ አካላት ጋር መክሯል፡፡

የ2013 በጀት ዓመት የሥራ እድል ፈጠራ ዙሪያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ እድል ፈጠራ ምክር ቤት አባላት እና የከተማ አስተዳደሩ ሁለቱም ምክትል ከንቲባዎች በተገኙበት ምክክር ተደርጓል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ እድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዞች ቢሮ ኃላፊ ይመር ከበደ በበጀት ዓመቱ በአስሩም ክፍለ ከተሞች 280 ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች በተለያዩ ዘርፎች ሥራ ለመፍጠር በእቅድ ይዞ ባለፈው ሩብ ዓመት ከ42 ሺህ በላይ ለሚደርሱ ዜግች ሥራ መፈጠሩን አስታውቀዋል፡፡ 173 ሺህ ሥራ ፈላጊዎችን የመለየት እና የመመዝገብ ሥራ መከናወኑንም አስረድተዋል፡፡ በከተማዋ ያሉ ፀጋዎች ልየታም ተሠርታል፡፡

በከተማዋ ባሉ ኢንተርፕራይዞች 216 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ሥራ መፍጠር የሚችል አቅም መኖሩ በውይይ ተነስቷል። በከተማ አስተዳደሩ 11 ሺህ 97 የሚደርሱ አንቀሳቃሽ ኢንተርፕራይዞች ውስጥ 166 ሺህ በላይ ለሚሆኑት ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል መፈጠሩም ነው የተመላከተው። በዚህ ዘርፍ 92 ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች ተጨማሪ የሥራ እድል መፍጠር የሚቻል ቢሆንም የመሥሪያ ቦታ እጦት፣ የማስፋፊያ ጥያቄ፣ የገበያ ትስስር አለማደግ፣ የፋይናንስ እና የብድር አቅርቦት ማነስ፣ ጸጋን ላይቶ ወደ ሀብት መቀየር አሁንም ከተማ አስተዳደሩ ያልተሻገራቸው ችግሮች በሚል በውይይቱ ተነስቷል፡፡

የመሪዎች ወጥ ግንዛቤ አለመኖር እና የዘመቻ ሥራ ላይ መጠመድ፣ ኮሮናቫረስ ወረርሽኝ፣ ሥራ ፈጣሪ ተቋማት ላይ ያለው ሥራ የመፍጠር አቅም ውስንነት፣የመብራት እና ትራንስፎርመር ክፍተት፣ አዳዲስ አሠራርን አለመዘርጋት፣ የተወሰደን ብድር የመመለስ ልምድ እጅግ ዝቅተኛ መሆን አሁንም ለዘርፉ ፈተና ሆነው ታይተዋል።

የኮሮናቫይረስ ጫና፣ ወቅታዊ የነበሩ የፀጥታ ችግሮች፣ መሠረተ ልማት በተላይ የመብራት ችግር፤ የብድር አቅርቦትና አመላለስ ላይ ያለው ክፍተት ለአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ከብሔራዊ ባንክ ተጨማሪ ብድር መበደር የማይችልበት ደረጃ መድረሱ ሰፊ ክፍተት ተብሎ ተነስቷል። የገበያ ትስስር አለመፍጠር ኢንተርፕራይዞች 5 ዓመት ሲሞላቸው በተቀመጠው ሕግ መሠረት አለማሸጋገር፣ ጠንካራ ተቋማዊ አሠራር አለመዘርጋት፣ የግብዓት ችግር፣ ሥራ ፈጣሪ ተቋማትን እቅድ ማስያዝ እንጅ ትኩረት ሰጥቶና ተናብቦ በተያዘው ውል መሠረት ሥራ እንዲፈጥሩ ማድረግ ላይ ያለ ክፍተት እንቅፋት ተብለው ተለይተዋል፡፡

አቶ አዲስ ዓለማየሁ የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ኃላፊ ናቸው፤ 267 ሚሊዮን ብር ለማሰመለስ ታቅዶ 245 ሚሊዮን እንዳስመለሱና ለወጣቶች ያለዋስትና የተሰጠውን ተዘዋዋሪ ብድር ማስመለስ ግን ፈተና እንደሆነባቸው አስታውቀዋል፡፡ የብድር አሰጣጥ እና አመላለስ ላይ የወጣው የብድርና አመላለስ መመሪያ አዲስ አበባ ላይ አልተተገበረም ባለፈው ዓመት 2 ቢሊዮን ብር ብድሩን በመታወቂያ ብቻ እንድንሰጥ መደረጉ ወጣቶችን አግኝተን ማስመለስ አልተቻለም ብለዋል ኃላፊው።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር ዓባይ ‘‘ያለፈውን ከመውቀስ ወጥተን ከችግሩ ተምረን በሥራ እድል ፈጠራ ዘርፍ ብዙ መሥራት አለብን፤ ለዚህ ደግሞ በብድር የተሰጡ ብድሮችን ማስመለስ አለብን’’ ብለዋል፡፡

‘‘የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን አሁንም ያላሳካነው ዘርፍ ነው። ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥም የግድ የዚህን ዘርፍ ይበልጥ ማሳደግ አለብን። በዚህ ላይ የተቀናጀ ሥራ መሠራት ይጠይቃል። ውኃ እና መብራት ላይ ያለውን ችግር ትኩረት ሰጥተን እንፈታለን። የፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሽፕ በተጠናከረ መልኩ ካልሠራን እቅዱን ማሳካት አንችልም እና በትኩረት ሊሠራ ይገባል’’ ብለዋል አቶ ጃንጥራር።

ምክትል ከንቲባዋ አዳነች አቤቤ ዘርፉ ለሁሉም የፖለቲካ፣ የሰላም እና የማህበራዊ ጉዳያችን ዋስትና በመሆኑ ትኩረት ሰጠን ልንሰራ ይገባልም ብለዋል፡፡ የብድር ማስመለስ ስራውን በትኩረት ይፈጸም ብለው የተዘዋዋሪም ሆነ የመደበኛ ብድር አሰጣጥ እና አመላለስ ላይ በትኩረት ይሰራል።

የሴቶች የሥራ እድል በጣም አናሳ በመሆኑ በቀጣይ ሊሠራ እንደሚገባ ያሳሰቡት ምክትል ከንቲባዋ ኢንተርፕራይዞችን ከ5 ዓመት በኋላ የማሸጋገር ሥራው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፈጸም እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡ ማራዘም አስፈላጊ ከሆነም በተጨባጭ መረጃ ሊሆን እነደሚገባም አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ጋሻው ፋንታሁን -ከአዲስ አበባ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየበረሃ አንበጣ መንጋን የመከላከል ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጥሪ አቀረቡ፡፡
Next articleበኢትዮጵያ እየተስፋፋ እና ጉዳት እያደረሰ ያለውን የበርሃ አንበጣ መንጋ ለመቆጣጠር ጠንካራ ርብርብ እያደረገ መሆኑን የፌዴራል ግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡