
ባሕር ዳር፡ መስከረም 27/2013ዓ.ም (አብመድ) የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ ስርጭት አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ በደረሱ ሰብሎች ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ኅብረተሰቡ የመከላከል ዘመቻው አካል እንዲሆን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በግብርና ሚኒስቴር የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ መከላከል ቴክኒክ ቡድን ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ተወያይተዋል፡፡
እንደ ቴክኒክ ቡድኑ ገለፃ በአሁኑ ወቅት የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ ስርጭት ፈጣን እና ሰፊ መሆኑ የመከላከል ሥራውን እጅግ ፈታኝ አድርጐታል፡፡
አሁን ካለበት ሁኔታ አንፃር የመከካል ሥራው ኬሚካል በሚረጩ አውሮፕላኖች መታገዝ ስላለበት ከጐረቤት ሀገራት ለበረሃ አንበጣ መንጋ ማጥፊያ የሚያገለግሉ አውሮፕላኖችን በድጋፍ ለማግኘት የተለያዩ ጥረቶች በመደረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ ደግሞ የአንበጣ ወረርሽኝ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ እና ለመከላከል የተጀመሩ ጥረቶች መጠናከር እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የበረሃ አንበጣ መንጋ ወረርሽኝ ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት እና በስፋት መጨመሩ በደረሱ ሰብሎች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት አሳሳቢ መሆኑን አንስተዋል፡፡ መንግሥት ችግሩን ለመከላከል የጀመረው ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በመጠቆም፤ ኅብረተሰቡም የመከላከል ዘመቻው አካል እንዲሆንም ጥሪ ማቅረባቸውን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m