የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አራተኛ የወንጀል ችሎት የሰኔ 15 ጥቃት ምስክሮችን ከሰዓት በኋላ መስማት ይጀምራል፡፡

472

ባሕር ዳር፡ መስከረም 27/2013ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አራተኛ የወንጀል ችሎት የሰኔ 15 ቀን 2011ዓ.ም የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ግድያን በተመለከተ ክስ የተመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎች ላይ የዐቃቢ ሕግ ምስክሮችን ዛሬ ከሰዓት በሚሰዬመው ችሎት መስማት ይጀምራል፡፡

ፍርድ ቤቱ ዛሬ መስከረም 27 ቀን 2013ዓ.ም በጠዋት በሚሰዬመው ችሎት የዐቃቢ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም በኮሮናቫይረስ ምክንያት ዐቃቢ ሕግ ለጥቂት ተከሳሾች ብቻ ምስክሮችን አስይዞ ስለነበር ዛሬ ላይ ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመነሳቱ ሁሉም ተከሳሾች ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲከታተሉ ስለተፈቀደ፣ ዐቃቤ ሕግ ሌላ ‘‘ጭብጥ እንዳስይዝ ለከሰዓት ቀጠሮ ይሰጠኝ’’ ብሎ በመጠዬቁ፤ ዐቃቢ ሕግ ያቀረብኳቸው ምስክሮች ከአሁን በፊት ከተመረጡት ተከሳሾች በተጨማሪ ለሌሎችም ሊመሰክሩ የሚችሉበት አግባብ ስለሚኖርም ብሎ ለፍርድ ቤቱ ጠይቋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በማረሚያ ቤት ውስጥ ሆነው ጉዳያቸውን ከሚከታተሉ ተከሳሾች መካከል አንደኛው ተከሳሽ በሥነ ምግባር ግድፈት ወደ ዳንግላ ማረሚያ ቤት በመዛወሩና በችሎት ላይ ባለመገኜቱ ምስክሮች ተከሳሺ በሌለበት መመስከር አይችሉም በመባሉ ነው፡፡ ዐቃቢ ሕግም ፍርድ ያላገኜ ታራሚ የማረሚያ ቤት ለውጥ ሊደረግለት እንደማይገባና ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶ ባለበት ማረሚያ ቤት መቆዬት ስላለበት ለማረሚያ ቤት ትዕዛዝ እንዲሰጥ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱም ታራሚውን በችሎት ቀጠሮ ቀን የማቅረብ ግዴታ የማረሚያ ቤት መሆኑን በማሳሰብ ታራሚው ከተቻለ ዛሬ ከሰዓት በሚኖረው ችሎት ካለበለዚያ ግን ነገ በሚኖረው ችሎት መቅረብ እንዳለበት ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ እነዚህን ምክንያቶች የሰማው ችሎቱም የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ለዛሬ ከሰዓት ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ሰኔ 15 ቀን 2011ዓ.ም በአማራ ክልል በተፈፀመ ጥቃት የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንንን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የፀጥታ አካላት መገደላቸው ይታወሳል፡፡ ፍርድ ቤቱም በዚህ ግድያ ላይ የተሳተፉ 55 ተጠርጣሪዎች ላይ ነው የዐቃቢ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ቀጠሮ የያዘው፡፡

ከ55ቱ ተጠርጣሪዎች መካከል 49ኙ በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው የሚከታተሉ ናቸው፡፡ ቀሪ ስድስቱ ደግሞ ያልተያዙ ናቸው ተብሏል፡፡ ፍርድ ቤቱም ያልተያዙት ተጠርጣሪዎች እንዲቀርቡ በጋዜጣ ጥሪ ያደረገ ቢሆንም አለመቅረባቸው ነው የተነገረው፡፡ ስለሆነም ፍርድ ቤቱ ባልቀረቡት ስድስቱ ተጠርጣሪዎች ላይ የክስ ሂደቱ በሌሉበት ይታያል ነው ያለው፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“ሰው የምንስበውም፤ የምንገፋውም እኛው ነን…” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ
Next articleየፌዴሬሽን ምክር ቤት በትግራይ ክልል መንግሥት ላይ ያሳለፈው ውሳኔ ተገቢና ትክክለኛ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት አስታወቀ።