
ባሕር ዳር፡ መስከረም 27/2013ዓ.ም (አብመድ) የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የእንቅስቃሴ ገደብ በተጣለበት ወቅት የጎዳና ተዳዳሪዎች መጠለያ ሆነው የቆዩ ትምህርት ቤቶችን ከከተማ አስተዳደሩ ጤና መምሪያ ጋር በመቀናጀት የፀረ ተህዋስያን ኬሚካል ርጭት ማድረግ መጀመሩን አስታውቋል፡፡ መምሪያው የ2013ዓ.ም የትምህርት ዘመንን ትምህርት ለማስጀመር ቅድሚያ መከናወን ካለበት ውስጥ አንዱ የፀረ ተህዋስያን ርጭት መሆኑን የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ተሻገር አዳሙ አስረድተዋል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ 52 የመንግሥት እና 46 የግል ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ተሻገር ቀደም ሲል የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የእንቅስቃሴ ገደብ በተጣለበት ወቅት የጎዳና ተዳዳሪዎች መጠለያ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩ አራት ትምህርት ቤቶችን ማለትም ግዮን አጠቃላይ 2ኛ ደረጃና መሠናዶ ትምህርት ቤት፣ ጣና ሐይቅ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃና መሠናዶ ትምህርት ቤት፣ ፋሲሎ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ባሕር ዳር የከፍተኛ ትምህርት መሠናዶ የፀረ ተህዋስያን ርጭት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ ሰሞኑን ሁሉም ትምህርት ቤቶች የፀረ ተህዋስያን ርጭት እንደሚደረግላቸውም ነው ኃላፊው የተናገሩት፡፡
‘’የፀረ ተህዋስያን ርጭት የሚያደርጉት ባለሙያዎች ከጤና ሚኒስቴር እና ከጤና ቢሮ ዕውቅና የተሰጣቸው ናቸው፡፡ የፀረ ተህዋስያን ርጭት ሊያጠፋ የሚችለው የኮሮናቫይረስን ብቻ ሳይሆን ሸረሪትን ጨምሮ ሌሎች ነፍሳትን ለማጥፋት ያግዛል‘’ ያሉት አቶ ተሻገር ተማሪዎች ትምህርት ሲጀምሩ የወረርሽኙ መከላከያ ቁሳቁስ እንደሚሟሉላቸው ገለጸዋል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች ሁሉም በሁለት ፈረቃ ማስተማር እንደሚችሉ ያስረዱት ኃላፊው ከመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ግን 16 ብቻ በሁለት ፈረቃ ማስተማር እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ የተቀሩት ትምህርት ቤቶች በሦስት ፈረቃ ከ25 እስከ 30 ተማሪዎችን በአንድ ክፍል በመመደብ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንደሚጀመር አስገንዝበዋል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች መማር ማስተማር ከመጀመራቸው በፊት የፀረ ተህዋስያን ርጭት እንዲያደርጉ አቅጣጫ እንደተሰጣቸውም አቶ ተሻገር ገልጸዋል፡፡ ሁሉም ትምህርት ቤቶች የዓለም ጤና ድርጅት እና የጤና ሚኒስቴር ያስቀመጡትን የትምህርት ማስጀመር መመሪያ መተግበር እንደሚጠበቅባቸው ያስረዱት ኃላፊው በየደረጃው የተደራጀው ግብረ ኃይል ይህንን አፈጻጸም የሚከታተል መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ትምህርት እና ጤና ጎን ለጎን መሄድ ስላለባቸው ለትምህርት ቤቶች እገዛ እያደረጉ እንደሚገኙ የጠቆሙት ደግሞ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ኃላፊ አስማማው ሞገስ ናቸው፡፡ ሁሉም የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት ቤቶች ወረርሽኙን በመከላከል የመማር ማስተማር ሂደቱን እንደሚቀጥሉ አቶ አስማማው አሳስበዋል፡፡ ‘‘በትምህርት ቤቶች ውስጥ ‘ስኩል ሃይጅን’ የተባለ አሠራር ስላለን ይህን አሠራር በመከወን ነው የተማሪዎችን ጤና የምንጠብቀው፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ጤና መምሪያ ወደፊትም ቢሆን የተማሪዎችን ጤና ለማስጠበቅ ከትምህርት ቤቶች ጋር በጋራ ይሠራል’’ ብለዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ በ2013 የትምህርት ዘመን ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል 122 ሺህ 160 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑን ከመምሪያው ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡
ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m