መረጃዎች

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ታሪክ

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሢመሠረት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባሕል፣ ቱሪዝም እና ማስታወቂያ ቢሮ ውስጥ አንድ መምሪያ ኾኖ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ የክልሉ የዜና ማዕከል ኾኖ ያገለግል ነበር፡፡ ድርጅቱ በ1986 ዓ.ም. የሰው ኃይሉ ቁጥር ከ13 አይበልጡም ነበር፡፡ የሥራ መሳሪዎቹም አገልግሎት የሰጡ፣ ፍጥነት እና ጥራታቸው እምብዛም የኾኑ እና ለሥራ አስቸጋሪ ነበሩ፡፡

በወቅቱ ጋዜጠኞቹም ቢኾኑ የተሰባሰቡት ከኢትዮጵያ ሬዲዮ፣ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እና ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተመርጠው የተውጣጡ ናቸው፡፡ በዚያን ጊዜም በድምፅ፣ በፎቶ፣ በጽሁፍ እና በተንቀሳቃሽ ምስል የተዘጋጁት ዘገባዎች በስልክ፣ በፖስታ ቤት፣ በአውሮፕላን ተልከው ለታዳሚያን ይደርሱ ነበር፡፡

ታሕሳስ 7 ቀን 1987 ዓ.ም. ስለአማራ ክልል በጋዜጣ መረጃ ለሚያገኙ የሕትመት ብርሃን የታየበት ቀን ነው፡፡ በወቅቱም “በኩር” የሚል ስያሜ የተሰጠው ጋዜጣ ተመስርቷል፡፡ የስያሜው ቃል ትርጓሜም የመጀመሪያ እንደማለት ነው፡፡ ስምንት ገጽ ያለውን ሳምንታዊ ጋዜጣ ለማተም ጋዜጠኞቹ ጽሁፍ እና ፎቶግራፎችን በሙጫ አጣብቀው፤ ወደ ማተሚያ ቤት በፖስታ ቤት አዲስ አበባ ልከው፤ እንደገና በአውቶብስ ተጭኖ ለዞን እና ወረዳ አንባቢያን ይደርስ እንደነበር ታሪካዊ ዳራው ይዘክራል፡፡ የህትመቱ ይዘቶችም ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ዜና እና ዜና ትንታኔ እንዲሁም አስተማሪ እና አዝናኝ መጣጥፎች ነበሩ፡፡

የአማርኛ ቋንቋ አንባቢያን ብቻ ሳይኾኑ በአማራ ክልል የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦችም ስለክልሉ በማንበብ መረጃ እንዲያገኙ እና ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና ሚዛናዊ ዘገባዎችን እንዲከታተሉ በአዊኛ፣ በአፋን ኦሮሞ እና በኸምጣና ቋንቋ በየ15 ቀኑ የሚታተሙ ጋዜጦች ጥቅምት 1 ቀን 2003 ዓ.ም. ለሕትመት በቅተው መሰራጨት ጀምረዋል፡፡ ጋዜጦቹም የቼርቤዋ በአዊኛ፤ የሂርኮ በኦሮምኛ፣ የኸምጠዊከ በኸምጠኛ ቋንቋ የሚዘጋጁ ሲኾን የስርጭት መጠናቸውም ለ1 ሺህ አንባቢያን የሚደርስ ነበር፡፡ ይህ መኾኑም ብሔረሰቦቹ በቋንቋቸው ለመፃፍ እና ለመወያየት ዕድል ፈጥሮላቸዋል፡፡

አብዛኛው የክልሉ ሕዝብ ዘገባ ቢደርሰው የሚመርጠው በሬዲዮ እንደኾነ ጥናቶች አመለከቱ፡፡ ግንቦት 1989 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ሬዲዮ አገልግሎት የአየር ሰዓት በመከራየት ስርጭት ተጀመረ፡፡ “የአማራ ድምፅ” በሚል መጠሪያ ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት እስከ 2፡00 ሰዓት በየእለቱ የዜና መረጃ፣ የትንታኔ ዘገባዎች እና እያዝናኑ የሚያስተምሩ ዝግጅቶች ሲተላለፉበት ቆዩ፡፡ ስርጭቱ ከባሕር ዳር ከተማ በመኾኑ ሕዝቡ እና አመራሩ በቅርበት ስለሚናገሩበት መረጃውን በወቅቱ ለማስተላለፍ አግዟል፡፡

የአማራ ድምፅ ሬዲዮ ተደማጭነቱ በመጨመሩም ሰኔ 10 ቀን 1997 ዓ.ም. የስርጭት ሰዓቱ ከ1፡00 ስዓት ወደ 6፡00 ሰዓት አደገ፡፡ በ2001 ዓ.ም. ደግሞ በቀን ወደ 9፡00 ሰዓት ከፍ አለ፡፡ የብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖችም ለሬዲዮ አድማጮቻቸው በቋንቋቸው መረጃ እንዲደርሳቸው ጥቅምት 1 ቀን 1997 ዓ.ም በሳምንት የ15 ደቂቃ ስርጭት የጀመሩ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በሳምንት የ2፡00 ሰዓት ስርጭት በማዘጋጀት ዜና እና ፕሮግራሞችን እንዲሁም መረጃ ሰጭ፣ አስተማሪ እና አዝናኝ ዘገባዎችን እያስተላለፉ ነው፡፡

የአሁኑ አማራ ኤፍ.ኤም. ባሕር ዳር 96.9፤ የቀድሞው ኤፍ.ኤም ባሕር ዳር 96.9 ለአድማጭ ጆሮ የደረሰው ሚያዝያ 22 ቀን 1994 ዓ.ም ነበር፡፡ ስርጭቱን በ2፡00 ሰዓት የጀመረው ጣቢያው ከግንቦት 1 ቀን 1994 ዓ.ም ጀምሮ በቀን የ4፡00 ሰዓት (ጧት ከ3፡00 እስከ 5፡00 ከስዓት ከ8፡00 እስከ 10፡00) ስርጭቱን ቀጠለ፡፡ በ2001 ዓ.ም ዕለታዊ ስርጭቱ ወደ 6፡00 ሰዓት አድጓል፡፡ ከመጋቢት 2004 ዓ.ም ጀምሮ ስርጭቱን በቀን ወደ 24፡00 ሰዓት ከፍ አድርጓል፡፡ ከደሴ እና ከደብረ ብርሃን የኤፍ.ኤም ራዲዮ ጣቢያዎች ጋር ጥምረት በመፍጠር ተደራሽነቱን ማስፋት ችሏል፡፡

የኤፍ.ኤም ራዲዮ ጣቢያዎችን የማስፋፊያ ፕሮጀክት በተመለከተ በመጀመሪያው የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን የመርሐ ግብር ዓመታት አምስት ጣቢያዎችን ለመገንባት በተያዘው እቅድ መሠረት የሦስቱን ጣቢያዎች ግንባታ በተሳካ ሁኔታ ማከናወን ተችሏል፡፡ በዚህም መሠረት ኤፍ.ኤም ባሕር ዳር 96.9 (የዘጌ አራራት) መጋቢት 2004 ዓ.ም፣ የደሴ ኤፍ.ኤም 87.9 ጥቅምት 20/2005 ዓ.ም እና ኤፍ.ኤም ደብረ ብርሃን 91.4 ኅዳር 7/2007 ዓ.ም ጣቢያዎች ተጠናቅቀው አገልግሎት መስጠት በመጀመራቸው የክልሉን አብዛኛውን ክፍል ለመሸፈን የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል፡፡

ሬዲዮ ጣቢያዎቹ ሕዝቡ የሚናገርባቸው ጣቢያዎች እንዲኾኑ ለማስቻል ሰፊ ጥረት ተደርጓል፡፡ የአሁኖቹ የአማራ ኤፍ ኤም ደሴ እና የደብረ ብርሃን የኤፍ.ኤም ራዲዮ ጣቢያዎች ግንቦት 20/2006 ዓ/ም ጀምሮ በቀን የ3፡00 ሰዓት አካባቢያዊ ስርጭት በመጀመራቸው ኅብረተሰቡን በቅርበት ለማገልገል ተችሏል፡፡ በድርጅቱ የአገልግሎት ጥራት እና ተደራሽነት ማሻሻያ መሠረት ሁለቱም ጣቢያዎች እለታዊ ስርጭታቸውን ወደ 6፡00 ሰዓት አሳድገዋል፡፡

ሚያዝያ 19/1992 ዓ.ም. በሳምንት ለግማሽ ሰዓት ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የአየር ሰዓት ተከራይቶ ስርጭቱን የጀመረው የአማራ ቴሌቪዥን ነው፡፡ ከማንበብ እና ከማዳመጥ በተጨማሪ ተመልካቾችም መረጃው በወቅቱ እንዲደርሳቸው የተጀመረው ስርጭት የአማራ ክልልን የተፈጥሮ ሃብት ገጽታ፤ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ቅርስ እንዲሁም የምጣኔ ሃብት ገጸ-በረከት ለማስተዋወቅ ነው፡፡ በዚያው ዓመትም ከ30 ደቂቃ ወደ 1፡00 ሰዓት ከዚያም በኋላ ወደ 7፡00 ሰዓት የስርጭት ሰዓቱ አድጓል፡፡

የአማራ ቴሌቪዥን ከጥቅምት 16/2006 ዓ.ም. ጀምሮም ስርጭቱ ወደ 12፡00 ሰዓት ከፍ ብሏል፡፡ ከዚያም ወደ 18፡00 ሰዓት አድጎ መተላለፍ ጀመረ፡፡ በአሁኑ ወቅት የ24፡00 ሰዓት ስርጭት እያስተላለፈ ነው፡፡ የሚያስተላልፏቸው የዘገባ ይዘቶችም ሕዝብ እና መንግሥት ፊት ለፊት የሚነጋገሩበት፣ ችግሮች እየተነሱ መፍትሔ የሚፈለግበት፣ የክልልን ገፅታ እና የተፈጥሮ ሃብት ፀጋዎች የሚተዋወቁበት ናቸው፡፡ ሕዝባዊ መድረኮች የሚስተናገዱበት እና ክርክር እና ውይይት የሚደረግበት በመኾኑም ታዳሚያን ጥልቀት ያላቸውን ትንታኔዎች በቀጥታ ያገኙበታል፡፡

የአማራ ብዙኅን መገናኛ ድርጅት ከ25 ዓመት በኋላ የሰው ኃይል ቁጥሩ ጨምሯል፡፡ በአሁኑ ወቅት 821 ሰራተኞች አሉት፡፡ ወንዶች 564 ሴቶቹ 257 ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ 443 ጋዜጠኞች፡፡ 121 የሚዲያ ቴክኖሎጅ ባለሙያዎች እና 186 የአስተዳደር ሠራተኞች ናቸው፡፡ ይህ የሰው ኃብቱ የትምህርት ዝግጅቱም ራዕዩን ለማሳካት እና ተግባሩን ለመወጣት ያስችሉታል፡፡ 65ቱ ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው ናቸው፡፡ 569ኙ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ 119 የሚኾኑት ዲፕሎማ እና የቴክኒክና ሙያ ተምረዋል፡፡

የአማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጅት በሰው ኃብት ብቻ ሳይኾን በዘመናዊ መሳሪያዎችም ተደራጅቷል፡፡ ከኪራይ የአየር ሰዓት ወጥቶ የራሱን ስቱዱዮ እና ማሰራጫ ገንብቷል፡፡ በየብስ እና በአየር መጓጓዣ መረጃዎችን በመላክ ያሰራጭ የነበረው አሁን ግን በሳተላይት እና በማቀባበያ እንዲሁም በድረ ገጽ እና በበይነ መረብ እያሰራጨ ነው፡፡ የሕትመት ውጤቶቹም የጥራት ደረጃ ጉድለቶቻቸው ተሻሽሎ የጽሁፍ እና የፎቶ እንዲሁም የገጽ ንድፍ ውበታቸው ከሞላ ጎደል ሳቢ እና ማራኪ ኾኗል፡፡ ከማዕከል ወደ ዞን እና ወረዳዎች ወርዶ ዘገባዎችን ከአካባቢው ለአካባቢው ለማድረስም የቅርንጫፍ ጣቢያዎች ተቋቁመዋል፤ አዳዲሶችም እየተከፈቱ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት የአማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጅት ለሁሉም ታዳሚዎቹ መረጃዎችን ለመስጠት እና ለመቀበል የሚገለገልባቸው ብዙኃን መገናኛዎች፡- የአማራ ሬዲዮ፣ የአማራ ቴሌቪዥን፣ አማራ ኤፍ ኤም ባሕር ዳር 96.9፣ አማራ ኤፍ ኤም ደሴ 87.9 እና አማራ ኤፍ ኤም. ደብረ ብርሃን 91.4፣ የበኩር ጋዜጣ እና የሦስቱ ብሔረሰብ ጋዜጦች (ኸምጠዊከ፣ ቸርቤዋና ሄርቆ) ሲሆኑ የተደራሽነት አደረጃጀት እና አገልግሎታቸውም እንደሚከተለው ነው፡፡
የአማራ ሬዲዮ፡- በመካከለኛ ሞገድ 801 KHZ እና በአጭር ሞገድ 6090 KHZ እንዲሁም በናይልሳት ተደራሽ በኾነባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ አድማጮች አስተማሪ እና አዝናኝ ዜና እና ኘሮግራሞች በአማርኛ ቋንቋ እንዲሁም በሦስቱ የብሔረሰብ ቋንቋዎች በየዕለቱ ለ18፡00 ሰዓታት የዘገባ ስራዎቹን ያቀርባል፡፡ በአማራ ሬዲዮ የሚቀርቡ የዘገባ ስራዎች በድርጅቱ ባለሙያዎች ከሚዘጋጁት በተጨማሪ በተባባሪ አካላትም በተያዙ የአየር ሰዓታት ዘገባዎች የአድማጭን ቀልብ የሚስቡ ኾነው ቀጥለዋል፡፡

አማራ ኤፍ ኤም ባሕር ዳር 96.9፣ አማራ ኤፍ ኤም ደሴ 87.9 እና አማራ ኤፍ ኤም ደብረ ብርሃን 91.4 MHZ ጣቢያዎች ዘወትር በቀን 16፡00 ሰዓታት እያዝናኑ የሚያስተምሩ ዜና እና ኘሮግራሞች ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ አሁንም በኤፍ.ኤም የራዲዮ ዘርፍ ያለውን የስርጭት ተደራሽነት ለማስፋፋት ከአማራ ኤፍ.ኤም ባሕር ዳር 96.9 እና ለዜና ደግሞ ከአማራ ሬዲዮ ስርጭት ለአማራ ኤፍ.ኤም 87.9 እና ለአማራ ኤፍ ኤም ደብረ ብርሃን 91.4 ራዲዮ ጣቢያዎች በጥምረት /Link/ በማድረግ የስርጭት ሰዓቱን ወደ 24፡00 ሰዓታት በማሳደግ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

ከአማራ ኤፍ.ኤም ደሴ 87.9 ጋር በማገናኘትም በቅብብሎሽ ዘዴ ለወልድያ እና አካባቢው እንዲሁም ከባሕር ዳር ኤፍ.ኤም 96.9 ጋር በማገናኘት ለደብረ ማርቆስ እና አካባቢው ዜናና ኘሮግራሞችን ማድረስ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም በአማራ ኤፍ ኤም ደሴ 87.9 እና በአማራ ኤፍ ኤም ደብረ ብርሃን 91.4 ጣቢያዎች አካባቢያዊ ዕለታዊ ስርጭት ለ6፡00 ሰዓታት ይሰራጫል፡፡

የአማራ ቴሌቪዥን፡- የአድማጭ ተመልካቹን ፍላጐት ይበልጥ ለማርካት አስተማሪ እና አዝናኝ ፕሮግራሞችን በየዕለቱ ለ24፡00 ሰዓታት እያሰራጨ የሚገኝ ሲኾን ተመራጭነቱን ለማሳደግም የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያዎችን አካሂዶ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ በጥናት ላይ ተመስርቶ በተደረገው ማሻሻያ መሰረትም ቀደም ሲል የአማራ ቴሌቪዥን ዜና እና ፕሮግራሞች በሚል ተደራጅቶ በአንድ የሥራ ሂደት ይከናወን የነበረውን አሰራር እንደገና የአማራ ቴሌቪዥን ዜና እና ስፖርት ዋና የስራ ሂደት እንዲሁም የአማራ ቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ዋና የስራ ሂደት በሚል በሁለት ሂደቶች ተደራጅቶ አሰራሩን ይበልጥ ለማዘመን ጥረት በማድረግ ላይ ነው፡፡
በዚህም መሰረት የዜናዎች ይዘትና አቀራረብ፣ የፕሮግራሞች ተደማጭነት እና በአጠቃላይ የአማራ ቴሌቪዥን ከሌሎች አቻ ሚዲያዎች ጋር ተወዳዳሪ እና ተመራጭ ሊሆን እንዲችል የሚያስችሉ ማሻሻያዎችን አድርጐ መረጃን በማድረስ ላይ ይገኛል፡፡

የበኩር ጋዜጣ በዜና እና መጣጥፍ አምዶቹ ዋና የሥራ ሂደ፡- በሳምንት አንድ ጊዜ ከ9500 በላይ ቅጅዎች በማተምና በማሰራጨት፣ ለአንባቢያን የክልሉን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ክንዋኔዎችን የተመለከቱ መረጃዎችን ተደራሽ እያደረገ ይገኛል፡፡

የደንበኞች አገልግሎት እና ኤፍ ኤም ጣቢያዎች ማስተባበሪያ፦ ማስተባበሪያው በተደረገው የአደረጃጀት ማሻሻያ መሠረት በአዲስ መልኩ ዜናዎችን በተደራጀ እና ወጥ በኾነ አካሄድ ለመተግበር ታስቦ የተዋቀረ ነው፡፡ ዳይሬክቶሬቱ በክልሉ ከሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች የሚመጡ ገቢ ዜናዎችን በመገምገም ለዜና ግብዓት የሚውሉትን ባለው የሰው ኃይል የአርትኦት ሥራ ሰርቶ ለሚዲዬሞች ያቀርባል፡፡ የዘገባ ጥቆማዎችን በማደራጀት ለኤዲቶሪያል ኮሚቴው በማቅረብም ሊዘገቡ የሚገባቸውን ስምሪት እንዲሰጥባቸው ያደርጋል፡፡ ከሕብረተሰቡ የሚነሱ ቅሬታዎችም በጥናት ላይ ተመስርተው ምላሽ እንዲያገኙ እያደረገ ነው፡፡

የቋንቋዎች ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት (አሚኮ ኅብር)፦ ዳይሬክቶሬቱ የክልሉን ብሄረሰብ ቋንቋዎች እና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ቡድን በጋራ በመያዝ የተደራጀ ነው፡፡ ዳይሬክቶሬቱ ከየብሄረሰቡ አስተዳደሮች ጋር የተያያዙና አጠቃላይ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ዜናና ፕሮግራሞችን እንዲሁም መጣጥፎችን በማሳተም እያሰራጨ ይገኛል፡፡ በእቅዱ መሰረት በዋናነት በብሄረሰብ አስተዳደሮች የሚካሄዱ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊና ማህበራዊ ጭብጦችን መሰረት አድርጎ መረጃዎችን በማሰባሰብ ለህትመት እና ለሬዲዮ ስርጭት አብቅቷል፡፡ በቴሌቭዥንም በተቀመጠው አሰራር መሰረት ታዳሚዉን ታሳቢ ያደረጉ ዜናና ፕሮግራሞችን በትርጉምና በዕቅድ በመስራት በማሰራጨት ላይ ነው፡፡

የብሮድካስት ኢንጅነሪንግና የፕሮዳክሽንና ስርጭት ኦፕሬሽን ዳይሬክቶሬት፡- ዳይሬክቶሬቶቹ በየጊዜው አደረጃጀታቸውን በማሻሻል መረጃን በጥራትና በፍጥነት ለማድረስ የብሮድካስት ሚዲዬሞችን ስርጭት በማዘመንና ብልሽት ሲገጥማቸው የማስተካከያ ጥገናዎችን በማድረግ ጥራታቸውን የጠበቁ ዘገባዎችን ለስርጭት በማብቃት እንቅስቃሴ አድርገዋል፡፡

በመገንባት ላይ ባሉት በአማራ ኤፍ.ኤም. ጎንደርና በአማራ ኤፍ ኤም ደብረ ማርቆስ የኤፍ. ኤም. ሬዲዮ ጣቢያዎች የመሳሪያ ተከላና ሌሎች ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡ በላልይበላ፣ በመተማና በወልዲያ የኤፍ.ኤም ጣቢዎች ስርጭቶች በጥራት እንዲደመጡም የማቀባበያ መሳሪያዎች ተተክለው አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡

የቀረፃና ቅንብር ዳይሬክቶሬት፡- የካሜራ ምስልና ድምፅ ቀረፃ እንዲሁም የምስልና ድምፅ ቅንብር ስራዎችን በማከናወን ጥራትን ለማምጣት እየሠራ ነው፡፡ የዜና፣ የዜና ሐተታ፣ የዘጋቢ ዘገባዎችን፣ የምርመራ ዘገባዎችንና ልዩ ልዩ ፕሮግራሞችን ምስልና ድምፅ እየቀረጸ መረጃ ይሰበስባል፡፡ ከመስክና ከስቱዱዮ የተቀረፁ ምስልና ድምፆችን ለዜና፣ ለፕሮግራም፣ ለቀጥታ ስርጭቶች ለዘጋቢ ዘገባና ለምርመራ ዘገባዎች ጥራት ያላቸውን ቅንብሮች ይሰራል፡፡

የኦን ላይንና ሞኒተሪግ ዋና የሥራ ሂደት፡- በአዲስ የሥራ ክፍል የተዋቀረው የኦን ላይንና ሞኒተሪንግ ዋና የስራ ሒደት በድረ ገፅና በማሕበራዊ ሚዲያ አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ በፅሁፍ፣ በፎቶ እና በተንቀሳቃሽ ምስል ዘገባዎችን በማጠናቀር ደንበኞቹን እያገለገለ ነው፡፡

ዳይሬክቶሬቱ እንደ አዲስ በተደራጀበት አንድ ዓመት ውስጥ ከድረ ገፅ በተጨማሪ በማሕበራዊ ሚዲያ ማለትም በፊስ ቡክ፣ በትዊተር፣ በዩትዩብና በሌሎችም መረጃ ማሰራጫዎች ዜናና መጣጥፍ እንዲሁም የድምፅ ዜናዎችን በማዘጋጀት ለታዳሚያን አድርሷል፡፡

የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት፡-አገራዊ ጉዳዮችን በቅርበትና በወቅቱ ለመዘገብ እንዲሁም የጎረቤት ክልሎችን ሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ እየቃኙ መረጃ ለመለዋወጥ የተቋቋመው ቅርንጫፉ ወቅታዊ ዜናዎችን፣ ጥልቀትና ብስለት ያለው ሙያዊ ትንታኔ የሚሰጡ ባለሙያዎችን እንዲሁም አገራዊ ጉዳዮችን ከክልሉ ምጣኔ ሐብታዊ፣ ፖለቲካዊና ማሕበራዊ ጉዳዮች ጋር በማስተሳሰር ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ታዳሚያን መረጃዎችን ያደርሳል፡፡

የአሚኮ ሥልጠናና ምርምር ማእከል፡- የአሚኮን እቅድ በማዘጋጀት፣ የአፈፃጸም ሪፖርትም በማሰናዳት ያቀርባል፡፡ የከፐርፖሬሽኑን የዘገባ አዘገጃጃትና አቀራራብ ከአዘጋጋብ መመሪያው አንፃር ድክምትና ጥንካሬዎችን በመፈተሸ የመፍትሔ ሐሳብ ያመነጫል፡፡ የአሚኮ የሰው ሐብት ልማትና የክህሎት ክፍተትን በእርስ በርስ መማማር፣ በውስጥ አቅምና ከዩኒቨርስቲዎች ጋር በጋራ በመተባበር የአቅም ግባታ ሥልጠናዎችን ይሰጣል፡፡

አሚኮ ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት የሕዝብን ፍላጎት መሰረት አድርጎ በመስራት ለለውጡ መፋጠን አስተዋኦ አበርክቷል፡፡ በተለይ ደግሞ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ የተደረገውን የሕዝብ እንቅስቃና የሕግ ማስከበር ዘመቻ ውጤታማ እንዲሆን የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ በ2013 በጀት ዓመትም ድርጅቱን ከብዙኃን መገናኛ ድርጅት ወደ ኮርፖሬሽን ለማሳደግ ጥና ተደርጎ በዚህም መሰረት ወደ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከመጋቢት 3-2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራወዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምሯል፡፡