የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሲመሰረት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ባሕል ቱሪዝምና ማስታወቂያ ቢሮ ውስጥ አንድ መምሪያ ሆኖ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ የክልሉ የዜና ማዕከል ሆኖ ያገለግል ነበር፡፡ ድርጅቱ በ1986 ዓ.ም. የሰው ኃይሉ ቁጥር ከ13 አይበልጡም ነበር፡፡ የሥራ መሳሪዎቹም አገልግሎት የሰጡ፤ ፍጥነትና ጥራታቸው እምብዛም የሆኑና ለስራ አስቸጋሪ ነበሩ፡፡
በወቅቱ ጋዜጠኞቹም ቢሆኑ የተሰባሰቡት ከኢትዮጵያ ሬዲዮ፣ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተመርጠው የተውጣጡ ናቸው፡፡ በዚያን ጊዜም በድምፅ፣ በፎቶ፣ በፅሁፍና በተንቀሳቃሽ ምስል የተዘጋጁት ዘገባዎች በስልክ፣ በፖስታ ቤት፣ በአውሮፕላን ተልከው ለታዳሚያን ይደርሱ ነበር፡፡
ታሕሳስ 7 ቀን 1987 ዓ.ም. ስለአማራ ክልል በጋዜጣ መረጃ ለሚያገኙ የሕትመት ብርሃን የታየበት ቀን ነው፡፡ በወቅቱም “በኩር” የሚል ስያሜ የተሰጠው ጋዜጣ ተመስርቷል፡፡ የስያሜው ቃል ትርጓሜም የመጀመሪያ እንደማለት ነው፡፡ ስምንት ገፅ ያለውን ሳምንታዊ ጋዜጣ ለማተም ጋዜጠኞቹ ፅሁፍና ፎቶግራፎችን በሙጫ አጣብቀው፤ ወደ ማተሚያ ቤት በፖስታ ቤት አዲስ አበባ ልከው፤ እንደገና በአውቶብስ ተጭኖ ለዞንና ወረዳ አንባቢያን ይደርስ እንደነበር ታሪካዊ ዳራው ይዘክራል፡፡ የህትመቱ ይዘቶችም ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊና ምጣኔ ሐብታዊ ዜናና ዜና ትንታኔ እንዲሁም አስተማሪና አዝናኝ መጣጥፎች ነበሩ፡፡
የአማርኛ ቋንቋ አንባቢያን ብቻ ሳይሆኑ በአማራ ክልል የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦችም ስለክልሉ በማንበብ መረጃ እንዲያገኙና ወቅታዊ፣ ትክክለኛና ሚዛናዊ ዘገባዎችን እንዲከታተሉ በአዊኛ፣ በአፋን ኦሮሞና በኸምጥኛ ቋንቋ በየ15 ቀኑ የሚታተሙ ጋዜጦች ጥቅምት 1 ቀን 2003 ዓ.ም. ለሕትመት በቅተው መሰራጨት ጀምረዋል፡፡ ጋዜጦቹም የቼርቤዋ በአዊኛ፤ የሂርኮ በኦሮምኛ፣ የኸምጠ ዊከ በኸምጠኛ ቋንቋ የሚዘጋጁ ሲሆን የስርጭት መጠናቸውም ለ1000 አንባቢያን የሚደርስ ነበር፡፡ ይህ መሆኑም ብሔረሰቦቹ በቋንቋቸው ለመፃፍና ለመወያየት ዕድል ፈጥሮላቸዋል፡፡
አብዛኛው የክልሉ ሕዝብ ዘገባ ቢደርሰው የሚመርጠው በሬዲዮ እንደሆነ ጥናቶች አመለከቱ፡፡ ግንቦት 1989 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ሬዲዮ አገልግሎት የአየር ሰዓት በመከራየት ስርጭት ተጀመረ፡፡ “የአማራ ድምፅ” በሚል መጠሪያ ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት እስከ 2፡00 ሰዓት በየእለቱ የዜና መረጃ፣ የትንታኔ ዘገባዎችና እያዝናኑ የሚያስተምሩ ዝግጅቶች ሲተላለፉበት ቆዩ፡፡ ስርጭቱ ከባሕር ዳር ከተማ በመሆኑ ሕዝቡና አመራሩ በቅርበት ስለሚናገሩበት መረጃውን በወቅቱ ለማስተላለፍ አግዟል፡፡
የአማራ ድምፅ ሬዲዮ ተደማጭነቱ በመጨመሩም ሰኔ 10 ቀን 1997 ዓ.ም. የስርጭት ሰዓቱ ከአንድ ወደ ስድስት ሰዓት አደገ፡፡ በ2001 ዓ.ም. ደግሞ በቀን ወደ 9 ሰዓት ከፍ አለ፡፡ የብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖችም ለሬዲዮ አድማጮቻቸው በቋንቋቸው መረጃ እንዲደርሳቸው ጥቅምት 1-1997 ዓ.ም በሳምንት የ15 ደቂቃ ስርጭት የጀመሩ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በሳምንት የሁለት ሰዓት ስርጭት በማዘጋጀት ዜናና ፕሮግራሞችን እንዲሁም መረጃ ሰጭ፣ አስተማሪና አዝናኝ ዘገባዎችን እያስተላለፉ ነው፡፡
የአሁኑ አማራ ኤፍ.ኤም. ባሕር ዳር 96.9፤ የቀድሞው ኤፍ.ኤም ባሕር ዳር 96.9 ለአድማጭ ጆሮ የደረሰው ሚያዝያ 22 ቀን 1994 ዓ.ም ነበር፡፡ ስርጭቱን በሁለት ሰዓት የጀመረው ጣቢያው ከግንቦት 1 ቀን 1994 ዓ.ም ጀምሮ በቀን የአራት ሰአት (ጧት ከ3፡00 እስከ 5፡00 ከስዓት ከ8፡00 እስከ 10፡00) ስርጭቱን ቀጠለ፡፡ በ2001 ዓ.ም ዕለታዊ ስርጭቱ ወደ ስድስት ሰዓት አድጓል፡፡ ከመጋቢት-2004 ዓ.ም. ጀምሮ ስርጭቱን በቀን ወደ 24፡00 ሰዓት ከፍ አድርጓል፡፡ ከደሴ እና ከደብረ ብርሃን የኤፍ.ኤም ራዲዮ ጣቢያዎች ጋር ጥምረት በመፍጠር ተደራሽነቱን ማስፋት ችሏል፡፡
የኤፍ.ኤም ራዲዮ ጣቢያዎችን የማስፋፊያ ፕሮጀክት በተመለከተ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የመርሃ ግብር አመታት አምስት ጣቢያዎችን ለመገንባት በተያዘው እቅድ መሠረት የሦስቱን ጣቢያዎች ግንባታ በተሳካ ሁኔታ ማከናወን ተችሏል፡፡ በዚህም መሠረት ኤፍ.ኤም ባህርዳር 96.9 (የዘጌ አራራት) መጋቢት 2004 ዓ.ም፣ የደሴ ኤፍ.ኤም 87.9 ጥቅምት 20/2005 ዓ.ም እና ኤፍ.ኤም ደ/ብርሃን 91.4 ህዳር 7/2007 ዓ.ም ጣቢያዎች ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት በመጀመራቸው የክልሉን አብዛኛውን ክፍል ለመሸፈን የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል፡፡
ሬዲዮ ጣቢያዎቹ ሕዝቡ የሚናገርባቸው ጣቢያዎች እንዲሆኑ ለማስቻል ሰፊ ጥረት ተደርጓል፡፡ የአሁኖቹ የአማራ ኤፍ ኤም ደሴና የደ/ብርሃን የኤፍ.ኤም ራዲዮ ጣቢያዎች ግንቦት 20/2006 ዓ/ም ጀምሮ በቀን የሦስት ሰዓት አካባቢያዊ ስርጭት በመጀመራቸው ህብረተሰቡን በቅርበት ለማገልገል ተችሏል፡፡ በድርጅቱ የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ማሻሻያ መሠረት ሁለቱም ጣቢያዎች እለታዊ ስርጭታቸውን ወደ ስድስት ሰዓት አሳድገዋል፡፡
ሚያዝያ 19-1992 ዓ.ም. በሳምንት ለግማሽ ሰዓት ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የአየር ሰዓት ተከራይቶ ስርጭቱን የጀመረው የአማራ ቴሌቪዥን ነው፡፡ ከማንበብና ከማዳመጥ በተጨማሪ ተመልካቾችም መረጃው በወቅቱ እንዲደርሳቸው የተጀመረው ስርጭት የአማራን ክልል የተፈጥሮ ሐብት ገፅታ፤ ባሕላዊና ኃይማኖታዊ ቅርስ እንዲሁም የምጣኔ ሐብት ገፀ-በረከት ለማስተዋወቅ ነው፡፡ በዚያው ዓመትም ከ30 ደቂቃ ወደ አንድ ሰዓት ከዚያም በኋላ ወደ ሰባት ሰዓት የስርጭት ሰዓቱ አድጓል፡፡
የአማራ ቴሌቪዥን ከጥቅምት 16- 2006 ዓ.ም. ጀምሮም ስርጭቱ ወደ 12 ሰዓት ከፍ ብሏል፡፡ ከዚያም ወደ 18 ሰዓት አድጎ መተላለፍ ጀመረ፡፡ በአሁኑ ወቅት የ24 ሰዓት ስርጭት እያስተላለፈ ነው፡፡ የሚያስተላልፏቸው የዘገባ ይዘቶችም ሕዝብና መንግስት ፊት ለፊት የሚነጋገሩበት፤ ችግሮች እየተነሱ መፍትሔ የሚፈለግበት፤ የክልልን ገፅታ እና የተፈጥሮ ሐብት ፀጋዎች የሚተዋወቁበት ናቸው፡፡ ሕዝባዊ መድረኮች የሚስተናገዱበትና ክርክርና ውይይት የሚደረግበት በመሆኑም ታዳሚያን ጥልቀት ያላቸውን ትንታኔዎች በቀጥታ ያገኙበታል፡፡
የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ከ25 ዓመት በኋላ የሰው ኃይል ቁጥሩ ጨምሯል፡፡ በአሁኑ ወቅት 821 ሰራተኞች አሉት፡፡ ወንዶች 564 ሴቶቹ 257 ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ 443 ጋዜጠኞች፤ 121 የሚዲያ ቴክኖሎጅ ባለሙያዎች፤ 186 የአስተዳደር ሠራተኞች ናቸው፡፡ ይህ የሰው ሐብቱ የትምህርት ዝግጅቱም ራዕዩን ለማሳካትና ተግባሩን ለመወጣት ያስችሉታል፡፡ 65ቱ ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው ናቸው፡፡ 569ኙ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ 119 የሚሆኑት ዲፕሎማ፣ የቴክኒክና ሙያ ተምረዋል፡፡
የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በሰው ሐብት ብቻ ሳይሆን በዘመናዊ መሳሪያዎችም ተደራጅቷል፡፡ ከኪራይ የአየር ሰዓት ወጥቶ የራሱን ስቱዱዮና ማሰራጫ ገንብቷል፡፡ በየብስና በአየር መጓጓዣ መረጃዎችን በመላክ ያሰራጭ የነበረው አሁን ግን በሳተላይትና በማቀባበያ እንዲሁም በድረ-ገፅና በበይነ መረብ እያሰራጨ ነው፡፡ የሕትመት ውጤቶቹም የጥራት ደረጃ ጉድለታቸው ተሻሽሎ የፅሁፍና የፎቶ እንዲሁም የገፅ ንድፍ ውበታቸው ከሞላ ጎደል ሳቢና ማራኪ ሆኗል፡፡ ከማዕከል ወደ ዞንና ወረዳዎች ወርዶ ዘገባዎችን ከአካባቢው ለአካባቢው ለማድረስም የቅርንጫፍ ጣቢያዎች ተቋቁመዋል፤ አዳዲሶችም እየተከፈቱ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ለሁሉም ታዳሚዎቹ መረጃዎችን ለመስጠትና ለመቀበል የሚገለገልባቸው ብዙኃን መገናኛዎች፡- የአማራ ሬዲዮ፣ የአማራ ቴሌቪዥን፣ አማራ ኤፍ ኤም ባ/ዳር 96.9፣ አማራ ኤፍ ኤም ደሴ 87.9 እና አማራ ኤፍ ኤም. ደብረ ብርሃን 91.4፣ የበኩር ጋዜጣና የሶስቱ ብሄረሰብ ጋዜጦች (ኸምጠ ዊከ፣ ቸርቤዋና HIRKOO) ሲሆኑ የተደራሽነት አደረጃጀትና አገልግሎታቸውም እንደሚከተለው ነው፡፡
የአማራ ሬዲዮ፡- በመካከለኛ ሞገድ 801 KHZ እና በአጭር ሞገድ 6090KHZ እንዲሁም በናይልሳት ተደራሽ በሆነባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ አድማጮች አስተማሪና አዝናኝ ዜናና ኘሮግራሞች በአማርኛ ቋንቋ እንዲሁም በሶስቱ የብሄረሰብ ቋንቋዎች በየዕለቱ ለ18 ሰዓታት የዘገባ ስራዎቹን ያቀርባል፡፡ በአማራ ሬዲዮ የሚቀርቡ የዘገባ ስራዎች በድርጅቱ ባለሙያዎች ከሚዘጋጁት በተጨማሪ በተባባሪ አካላትም በተያዙ የአየር ሰዓታት ዘገባዎች የአድማጭን ቀልብ የሚስቡ ሆነው ቀጥለዋል፡፡
አማራ ኤፍ ኤም ባ/ዳር 96.9፣ አማራ ኤፍ ኤም ደሴ 87.9 እና አማራ ኤፍ ኤም ደብረ ብርሃን 91.4 MHZ ጣቢያዎች ዘወትር በቀን 16 ሰዓት እያዝናኑ የሚያስተምሩ ዜናና ኘሮግራሞች ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ አሁንም በኤፍ.ኤም የራዲዮ ዘርፍ ያለዉን የስርጭት ተደራሽነት ለማስፋፋት ከአማራ ኤፍ.ኤም ባህር ዳር 96.9 እና ለዜና ደግሞ ከአማራ ሬዲዮ ስርጭት ለአማራ ኤፍ.ኤም 87.9 እና ለአማራ ኤፍ ኤም ደብረ ብርሃን 91.4 ራዲዮ ጣቢያዎች በጥምረት /Link/ በማድረግ የስርጭት ሰዓቱን ወደ 24 ሰዓት በማሳደግ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
ከአማራ ኤፍ.ኤም ደሴ 87.9 ጋር በማገናኘትም በቅብብሎሽ ዘዴ ለወልድያና አካባቢው እንዲሁም ከባ/ዳር ኤፍ.ኤም 96.9 ጋር በማገናኘት ለደ/ማርቆስና አካባቢው ዜናና ኘሮግራሞችን ማድረስ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም በአማራ ኤፍ ኤም ደሴ 87.9 እና በአማራ ኤፍ ኤም ደብረ ብርሃን 91.4 ጣቢያዎች አካባቢያዊ ዕለታዊ ስርጭት ለ 6 ሰዓት ይሰራጫል፡፡
የአማራ ቴሌቪዥን፡- የአድማጭ ተመልካቹን ፍላጐት ይበልጥ ለማርካት አስተማሪና አዝናኝ ፕሮግራሞችን በየዕለቱ ለ24 ሰዓት እያሰራጨ የሚገኝ ሲሆን ተመራጭነቱን ለማሳደግም የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያዎችን አካሂዶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ በጥናት ላይ ተመስርቶ በተደረገው ማሻሻያ መሰረትም ቀደም ሲል የአማራ ቴሌቪዥን ዜናና ፕሮግራሞች በሚል ተደራጅቶ በአንድ የስራ ሂደት ይከናወን የነበረውን አሰራር እንደገና የአማራ ቴሌቪዥን ዜናና ስፖርት ዋና የስራ ሂደት እንዲሁም የአማራ ቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ዋና የስራ ሂደት በሚል በሁለት ሂደቶች ተደራጅቶ አሰራሩን ይበልጥ ለማዘመን ጥረት በማድረግ ላይ ነው፡፡
በዚህም መሰረት የዜናዎች ይዘትና አቀራረብ፣ የፕሮግራሞች ተደማጭነትና በአጠቃላይ የአማራ ቴሌቪዥን ከሌሎች አቻ ሚዲያዎች ጋር ተወዳዳሪና ተመራጭ ሊሆን እንዲችል የሚያስችሉ ማሻሻያዎችን አድርጐ መረጃን በማድረስ ላይ ይገኛል፡፡
የበኩር ጋዜጣ በዜናና መጣጥፍ አምዶቹ ዋና የሥራ ሂደ፡- በሳምንት አንድ ጊዜ ከ9500 በላይ ቅጅዎች በማተምና በማሰራጨት፣ ለአንባቢያን የክልሉን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ክንዋኔዎችን የተመለከቱ መረጃዎችን ተደራሽ እያደረገ ይገኛል ፡፡
የደንበኞች አገልግሎትና ኤፍ ኤም ጣቢያዎች ማስተባበሪያ፦ ማስተባበሪያው በተደረገው የአደረጃጀት ማሻሻያ መሰረት በአዲስ መልኩ ዜናዎችን በተደራጀና ወጥ በሆነ አካሄድ ለመተግበር ታስቦ የተዋቀረ ነው፡፡ ዳይሬክቶሬቱ በክልሉ ከሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች የሚመጡ ገቢ ዜናዎችን በመገምገም ለዜና ግብዓት የሚውሉትን ባለው የሰው ሀይል የአርትኦት ስራ ሰርቶ ለሚዲዬሞች ያቀርባል፡፡ የዘገባ ጥቆማዎችን በማደራጀት ለኤዲቶሪያል ኮሚቴው በማቅረብም ሊዘገቡ የሚገባቸውን ስምሪት እንዲሰጥባቸው ያደርጋል፡፡ ከሕብረተሰቡ የሚነሱ ቅሬታዎችም በጥናት ላይ ተመስርተው ምላሽ እንዲያገኙ እያደረገ ነው፡፡
የቋንቋዎች ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት (አሚኮ ኅብር)፦ ዳይሬክቶሬቱ የክልሉን ብሄረሰብ ቋንቋዎች እና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ቡድን በጋራ በመያዝ የተደራጀ ነው፡፡ ዳይሬክቶሬቱ ከየብሄረሰቡ አስተዳደሮች ጋር የተያያዙና አጠቃላይ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ዜናና ፕሮግራሞችን እንዲሁም መጣጥፎችን በማሳተም እያሰራጨ ይገኛል፡፡ በእቅዱ መሰረት በዋናነት በብሄረሰብ አስተዳደሮች የሚካሄዱ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊና ማህበራዊ ጭብጦችን መሰረት አድርጎ መረጃዎችን በማሰባሰብ ለህትመት እና ለሬዲዮ ስርጭት አብቅቷል፡፡ በቴሌቭዥንም በተቀመጠው አሰራር መሰረት ታዳሚዉን ታሳቢ ያደረጉ ዜናና ፕሮግራሞችን በትርጉምና በዕቅድ በመስራት በማሰራጨት ላይ ነው፡፡
የብሮድካስት ኢንጅነሪንግና የፕሮዳክሽንና ስርጭት ኦፕሬሽን ዳይሬክቶሬት፡- ዳይሬክቶሬቶቹ በየጊዜው አደረጃጀታቸውን በማሻሻል መረጃን በጥራትና በፍጥነት ለማድረስ የብሮድካስት ሚዲዬሞችን ስርጭት በማዘመንና ብልሽት ሲገጥማቸው የማስተካከያ ጥገናዎችን በማድረግ ጥራታቸውን የጠበቁ ዘገባዎችን ለስርጭት በማብቃት እንቅስቃሴ አድርገዋል፡፡
በመገንባት ላይ ባሉት በአማራ ኤፍ.ኤም. ጎንደርና በአማራ ኤፍ ኤም ደብረ ማርቆስ የኤፍ. ኤም. ሬዲዮ ጣቢያዎች የመሳሪያ ተከላና ሌሎች ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡ በላልይበላ፣ በመተማና በወልዲያ የኤፍ.ኤም ጣቢዎች ስርጭቶች በጥራት እንዲደመጡም የማቀባበያ መሳሪያዎች ተተክለው አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡
የቀረፃና ቅንብር ዳይሬክቶሬት፡- የካሜራ ምስልና ድምፅ ቀረፃ እንዲሁም የምስልና ድምፅ ቅንብር ስራዎችን በማከናወን ጥራትን ለማምጣት እየሠራ ነው፡፡ የዜና፣ የዜና ሐተታ፣ የዘጋቢ ዘገባዎችን፣ የምርመራ ዘገባዎችንና ልዩ ልዩ ፕሮግራሞችን ምስልና ድምፅ እየቀረጸ መረጃ ይሰበስባል፡፡ ከመስክና ከስቱዱዮ የተቀረፁ ምስልና ድምፆችን ለዜና፣ ለፕሮግራም፣ ለቀጥታ ስርጭቶች ለዘጋቢ ዘገባና ለምርመራ ዘገባዎች ጥራት ያላቸውን ቅንብሮች ይሰራል፡፡
የኦን ላይንና ሞኒተሪግ ዋና የሥራ ሂደት፡- በአዲስ የሥራ ክፍል የተዋቀረው የኦን ላይንና ሞኒተሪንግ ዋና የስራ ሒደት በድረ ገፅና በማሕበራዊ ሚዲያ አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ በፅሁፍ፣ በፎቶ እና በተንቀሳቃሽ ምስል ዘገባዎችን በማጠናቀር ደንበኞቹን እያገለገለ ነው፡፡
ዳይሬክቶሬቱ እንደ አዲስ በተደራጀበት አንድ ዓመት ውስጥ ከድረ ገፅ በተጨማሪ በማሕበራዊ ሚዲያ ማለትም በፊስ ቡክ፣ በትዊተር፣ በዩትዩብና በሌሎችም መረጃ ማሰራጫዎች ዜናና መጣጥፍ እንዲሁም የድምፅ ዜናዎችን በማዘጋጀት ለታዳሚያን አድርሷል፡፡
የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት፡-አገራዊ ጉዳዮችን በቅርበትና በወቅቱ ለመዘገብ እንዲሁም የጎረቤት ክልሎችን ሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ እየቃኙ መረጃ ለመለዋወጥ የተቋቋመው ቅርንጫፉ ወቅታዊ ዜናዎችን፣ ጥልቀትና ብስለት ያለው ሙያዊ ትንታኔ የሚሰጡ ባለሙያዎችን እንዲሁም አገራዊ ጉዳዮችን ከክልሉ ምጣኔ ሐብታዊ፣ ፖለቲካዊና ማሕበራዊ ጉዳዮች ጋር በማስተሳሰር ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ታዳሚያን መረጃዎችን ያደርሳል፡፡
የአሚኮ ሥልጠናና ምርምር ማእከል፡- የአሚኮን እቅድ በማዘጋጀት፣ የአፈፃጸም ሪፖርትም በማሰናዳት ያቀርባል፡፡ የከፐርፖሬሽኑን የዘገባ አዘገጃጃትና አቀራራብ ከአዘጋጋብ መመሪያው አንፃር ድክምትና ጥንካሬዎችን በመፈተሸ የመፍትሔ ሐሳብ ያመነጫል፡፡ የአሚኮ የሰው ሐብት ልማትና የክህሎት ክፍተትን በእርስ በርስ መማማር፣ በውስጥ አቅምና ከዩኒቨርስቲዎች ጋር በጋራ በመተባበር የአቅም ግባታ ሥልጠናዎችን ይሰጣል፡፡
አሚኮ ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት የሕዝብን ፍላጎት መሰረት አድርጎ በመስራት ለለውጡ መፋጠን አስተዋኦ አበርክቷል፡፡ በተለይ ደግሞ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ የተደረገውን የሕዝብ እንቅስቃና የሕግ ማስከበር ዘመቻ ውጤታማ እንዲሆን የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ በ2013 በጀት ዓመትም ድርጅቱን ከብዙኃን መገናኛ ድርጅት ወደ ኮርፖሬሽን ለማሳደግ ጥና ተደርጎ በዚህም መሰረት ወደ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከመጋቢት 3-2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራወዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምሯል፡፡
በ2022 በኢትዮጵያ ተደራሽ ከሆኑ ብዙኃን መገናኛ ተቋማት ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆኖ ማየት
ዕውነተኛና ተዓማኒ መረጃን በፍጥነት በማቅረብ የሐሳብ ነፃነት እንዲነቃቃ፣ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠርና ዲሞክራሲያዊ እሴቶች እንዲጎለብቱ አጋዥ ሚና መጫወት፤
ሀ.ሙያዊ መርህን ማክበር
ለ.ሕዝባዊ ወገንተኝነት
ሐ.ጥበባዊ ፈጠራ
መ.በጋራ መስራት
ዘገባዎች የተቋሙንና የሕዝቡን ክብር የጠበቁ እንዲሆኑ እናደርጋለን፡፡
ሕብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃዎች እንዲደርሱት በትጋት እንሰራለን፡፡
ሕዝቡ ትክክለኛ መረጃዎችን የማወቅ መብቱ እንዲከበር ለሙያዊ መርህ እንቆማለን፡፡
ዘገባዎች እሴቶቻቸውን ጠብቀው በፍጥነትና በወቅቱ ወደ ታዳሚያን እንዲደርሱ እናደርጋለን፡፡
በሁሉም የአገልግሎት አሰጣጥ ዘርፎች ሙያዊ መርህን እናከብራለን ፡፡
አገርን የሚጎዳ መረጃ አሳልፈን ላለመስጠት በሚስጥር እንጠብቃለን፡፡
ከየትኛውም ወገን የሚቀርቡ አስተያየቶችን ፍትሃዊና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ እናስተናግዳለን፡
የሕዝብን ጥቅም የሚያስከብሩ ስራዎችን በማከናወን ሕዝባዊ ወገንተኝነትን እናረጋግጣለን፡፡
የሕዝቦችን መብቶችና ነፃነቶችን የሚያስከብሩ ዘገባዎችን በብስለትና በጥልቀት እናቀርባለን፡፡
በሕዝቦች መካከል የእርስ በርስ መደጋገፍና መተባበርን የሚያበረታቱ እሴቶችን እናጎላለን፡፡
የመልካም ስነ-ምግባር መርሆዎችን ለሚተነትኑ ዘገባዎች ትኩረት እንሰጣለን፡፡
ለሕዝብ ልዕልና የሚቆሙ የዘገባ ስራዎችን ቀዳሚ ተግባሮቻችን አድርገን እንዘግባለን፡፡
በምርመራ ዘገባችን ምዝበራና የሀብት ብክነትን በማጋለጥ ተጠያቂነትን እናሰፍናለን፡፡
የዘገባችንን ይዘት አመራረጥ፣ አዘገጃጀትና አቀራረብ ሳቢና ማራኪ እናደርጋለን፤
የታዳሚያችንን ርካታና አመኔታ የሚያሳድሩ ፈጠራዎችን በዘገባ ስራችን ላይ በጥራት እንተገብራለን፤
ዘመናዊ ቴክኖሎጅዎች በመጠቀም የፈጠራ ስራችንን መልዕክት ግልፅ፣ ቀላልና ሳቢ እናደርጋለን፡፡
በፈጠራ የታገዙ ተዓማኒነት ያላቸው ዘገባዎችን በፍጥነትና በጥራት እናደርሳለን፤
የቡድን ሥራን በማጎልበት ተጋግዞ የመስራትን መርህ እንከተላለን፤
እርስ በርስ በመማማር ሙያችንን ለማሳደግ እንተጋለን፤
የጋራ ችግርን ተወያይቶ በጋራ በመፍታት መተማመንን እንፈጥራለን፤
ከሌሎች አጋርና ተባባሪ አካላት ጋር በጋራ ሠርተን ውጤት እናመጣለን፤
ለጋራ ውጤት በጋራ መንፈስ እንሰራለን የሚሉ ናቸው፡፡