የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ22ኛ ሳምንት የጨዋታ መርሐ ግብር ባሕር ዳር ከተማን ከሀዲያ ሆሳዕና ያገናኛል፡፡

0
202

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ22ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ። በ22ኛው ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ ከኢትዮጵያ መድኅን ከቀኑ 10 ሰዓት በድሬዳዋ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በአሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት የሚመራው ወልቂጤ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጨዋታ ሲኾን አንድ ጊዜ ሲሸነፍ በሦስቱ አቻ ተለያይቷል። ወልቂጤ በ16 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ላይ ይገኛል። ተጋጣሚው ኢትዮጵያ መድኅን ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ አንድ ጊዜ ተሸንፎ በቀሪዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። በገብረመድህን ኃይሌ የሚሰለጥነው ኢትዮጵያ መድኅን በ19 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ምሽት 1 ሰዓት በሚደረገው ሌላኛው የ22ኛ ሳምንት የጨዋታ መርሐ ግብር ባሕር ዳር ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ይገናኛሉ። ባሕር ዳር ከተማ ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ያልተሸነፈ ሲኾን በሦስቱ ሲያሸንፍ በሁለቱ አቻ ተለያይቷል። በአሠልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የሚመራው ባሕር ዳር ከተማ በ33 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሀዲያ ሆሳዕና በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሁለቱ ድል ሲቀናው በአንዱ ተሸንፎ በሁለቱ ነጥብ ተጋርቷል። በአሠልጣኝ ግርማ ታደሰ የሚመራው ሀዲያ ሆሳዕና በ30 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። የ22ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ነገም ሲቀጥል ፋሲል ከነማ ከአዳማ ከተማ ከምሽቱ 1 ሰዓት፣ ሀምበሪቾ ዱራሜ ከሃዋሳ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት ይጫወታሉ። የ22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እስከ ሚያዚያ 13/2016 ዓ.ም እንደሚቆይ ከመርሐግብሩ ለማወቅ ተችሏል።

ፕሪሚየር ሊጉን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ43 ነጥብ እየመራ ይገኛል። የሃዋሳ ከተማው አጥቂ አሊ ሱሌይማን 12 ጎሎች በማስቆጠር የፕሪሚየር ሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት እየመራ ነው። ዩጋንዳዊው የድሬዳዋ ከተማ ተጫዋች ቻርልስ ሙሲጌ፣ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አማኑኤል ኦርቦ፣ የባሕር ዳር ከተማው ቸርነት ጉግሳ እና የአዳማ ከተማው ዮሴፍ ታረቀኝ በተመሳሳይ በ9 ግቦች ይከተላሉ።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከ23ኛ እስከ 27ኛ ሳምንት የሚካሄዱ ጨዋታዎች በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እንደሚካሄዱ የሊጉ አክሲዮን ማኅበር ማስታወቁ ይታወሳል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here